የፌስቱላ ሀኪሟ አሸልባለች ። ሰው ማለትስ እንደ ሃምሊን! ስራዋቿ በልባችን ለዘላለም ይኖራሉ!






በአዲስ አበባ 61 አመት ከኖረችበት የስንቱን ሴት ስቃይ ካከመችበት ምድር ቤት በሰላም ወደ ወዲያኛው አለም ሄዳለች ። ኢሌን ካትሪን ሃምሊን ላትመለሰ ሄዳለች።

በለንደን የሚታተመው ላንሴት የህክምና ጆርናል መፅሄት ኢትዮጵያ ውስጥ 3 አመት መቆየት የሚፈልግ የፅንስ ህክምና ባለሙያ ይፈለጋል ብሎ ከዛሬ 62 አመት በፊት ያወጣው ማስታወቂያ ሲድኒ የምትኖረው በእዛም የሴቶች ሆስፒታል የምትሰራው ሃምሊን ከባሏ ጋር ሆና አነበበችው” ለምን አንሄድም አለችው ? ካልተመቸን እንመለሳለንም “አለችው ።

ባሏም ዶክተር ሪናልድ ሃምሊን በሚስቱ ሀሳብ ተስማማ ። ይዛውም አዲስ አበባ መጣች።
በአዲስ አበባም በንጉስ ሀይለስላሴ ልጅ በልዕልት ፀሀይ መታሰቢያ ሆስፒታል መስራት ጀመሩ ። ልዕልት ፀሀይ ለንደን በነርሰ ተምራ ወለጋ ካለ አንድ አስተዳዳሪ ጋር ተጋብታ ስትኖር የሞተችው በፅንስ ህመም ነበር ።ሀይለስላሴም ሆስፒታሉን በልጃቸው ሲሰይሙ ተመሳሳይ ህመም ያለባቸው ሴቶች አንዲታከሙበት በማሰብ ነበር።

የዛሬ 61 አመት ኢትዮጵያ የመጣችው ሃምሊን
ባየችሁ ነገር ደነገጠች ።”አዚህ ሀገር በፌስቱላ ብዙ ሰው ይሞታል “አሏት ። ፌስቱላም በተፈጥሯቸው ውስጣቸው ክፍት የሆኑ ሁለት የሰውነት ክፍሎችን የሚያለያየው አካል በጉዳት ሲበሳና ሁለቱን ክፍተቶች ሲያቀላቅል የሚከሰት የጤና ችግር ስንቱን ሲያስለቅስ ተመለከተች ።
ከዛም ባሏን እንዲህ አለችው ” አየህ አይደል ! ይቺ ሀገር ላይ በፌስቱላ ምክንያት ሴቶች የማህጸን በራቸው ከሽንትና ከሰገራ መውጫ ጋር ተቀላቅሎባቸው ሽንታቸውንም ሆነ ሰገራቸውን መቆጣጠር አቅቷቸው ለአካልና ለስነ ልቦና ጉዳት ሲዳረጉ! ።ይሄን እያዩ ወደ አውስትራሊያ ሲድኒ መመለስ እብደት ነው ።ሞራል ያለው ሰው ይሄን አያረገም “አለቸው ።
ባሏም በሚስቱ ሀሳብ ተስማማ ። በኢትዮጵያ የመጀመርያ የሆነውን ሃምሊን ኢትዮጵያ ፌስቱላ ሆስፒታሉን ባልና ሚስቱ በመኖርያ ቤታቸው ከፈቱ ።
ሆስፒታሉ ዛሬ አድጎ በአማራ፣በትግራይ ፣በደቡብ እና በኦሮሚያ ቅርንጫፎችን ከፈቷል ።አስከዛሬም ከ60,000 በላይ ሴቶችን አክሟል ።
በሃምሊን ሆስፒታል ህክምና ካገኙት መሀል አንዲት የ16 አመት ሴት ለአዲስ አድማስ ጋዜጣ እንዲህ ብላ ነበር “
” እዚህ የመጣሁት የፌስቱላ ታማሚ ሆኜ ነው፡፡ እድሜዬ አስራ ስድስት አመት ነው፡፡ መሔድ የማልችለው እግሬ ተሳስሮ አልሄድ ብሎ ነው፡፡ የመጣሁት ከጎንደር ሲሆን የህመሜ ምክንያት ወሊድ ነው፡፡ ምጥ ያመመኝ ለአራት ቀን ነው፡፡ በአካባቢዬ ያለው ሆስፒታል ሳይሆን ጤና ጣብያ ነው፡፡ እነርሱ ሊያዋል ዱኝ ስላልቻሉ ወደቤት እንድመለስ ተደረገ፡፡ በእርግጥ ጤና ጣቢያዎቹ ያማከሩን ሻል ወደአለ ሕክምና አገልግሎት እንድወድ ነበር፡፡ ነገር ግን ስለአልተቻለ ቤተ ሰቡ እያዘነ ወደቤት መልሰውኝ …ያው…በአራት ቀኑ በግድ ሕይወት የሌለውን ልጅ ተገላገልኩ፡፡ ከዚያ በሁዋላ ግን እግሬ መቆም አልቻለም፡፡ እንደገናም ሽንቱ እየፈሰሰ አስቸገረ፡፡ ቤተሰቦቼ ወደዚህ ያመጡኝ እግርዋ እንኩዋን ቢሄድ ብለው እንጂ ሽንቱስ ይድናል ብለው አይደለም፡፡ አባ ሕክምና አለ ሲሉት ወደባህር ዳር ሆስፒታል ይዞኝ ሲሄድ የባህርዳር ሆስፒታል ደግሞ ወደዚህ አመጣኝ፡፡ …ለካንስ ሕክምና ኖሮአል….” በማለት የሀምሊን ሆስፒታል አመስግናለች ።

ጠንካራዋ ሃምሊን በሆስፒታሉ አብሯት የሰራው ባሏን ከ26 አመት በፊት ሞተባት ።ትልቅ የመንፈስ ስብራት ነበር ።ለሁሉ ነገሯ ጀርባ ሆኖ ሲያግዝ የነበረን ሰው ማጣት ከባድም ነገር ነው ።ግን ሒይወት እንደዚህ ናት ።መራራ የሆነውንም ነገር ተቀብሎ የጀመሩትን ስራ ማጠናከር ።ሃምሊን ያን አደረገች ሆስፒታሉን ለብዙ ሴት ህክምና እንዲሰጥ በማድረግ በጎዋን ስራ ቀጠለችው ።

ሁለቴ ለኖቤል የሽልማት ታጭታ ነበር ።የኖቤል አቻ የሆነውን “ላይቭሊሁድ አዋርድ “ከስምንት አመት በፊት አግኝታለች ። በንጉስ ሀይለስላሴ ፣በመለስ ዜናዊ ፣ በአቶ ሀይለማርያምና ደሳለኝ እና በአሁኑ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ የተለያዮ ሸልማቶችና ሰርተክፌት አግኝታለች። የክብር ኢትዮጵያዊ ዜግነትም አግኝታለች ። ከ20 በላይ አለም አቀፍ ሽልማቶችም ተቀብላለለች ።በአሜሪካ ተወዳጅ በሆነው “ኦፕራ ሾው” ላይም ቀርባ ስለ ስራዋ አውራታለች ። አዲስ አበባ በስሟ በተሰየመው ፋውንዴሽን ጊቢ ውስጥ የባሏን እጅ ይዛ የሚየሳይ ሀውልት ቆሞላታል ። በሀውልቱ ምርቃት ላይ ጠ/ሚ ዐብይም ተገኝተው ነበር ። የወርቅ ሜዳሊያም አበርክተውላታል።
ሃምሊን በስጋ ነው የሞተችው ስራዎቸ ግን ለዘላለም ይኖራሉ። ተለክቶ የተሰጣትን ሒወት አላሾፈችበትም ። ባህር ተሻግራ በፌስቱላ የተሰቃዩ ደሀ ሴቶችን አክማበት የስንቱን ስቃይ አድና አስተምራን ነው በ96 አመቷ ትናንት እሮብ መጋቢት 9,2012 የሞተችው ።ሰውስ ማለት እንደ ሀምሊን ለሰው የሚኖር!


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *