======<< >>======
አሁን ባለንበት የዘመን መንፈስ . . .
በኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ስመጥር ጉምቱ ድምፃውያን ለአድናቂዎቻቸው አዲስ የሙዚቃ አልበም ለማበርከት “ጊዜ መራሽ ፍርሃት” እየተገዳደራቸው ስለመሆኑ በአደባባይ ሲናገሩ ይደመጣሉ።
ድምፃዊ #ነዋይ_ደበበ በቅርቡ ሰይፉ በ~EBS ላይ ቀርቦ . . . “እጅ ከምን?” ለሚሉት አድናቂዎቹ ለረጅም ዓመታት አዲስ አልበም ማበርከት ያልቻለበትን ምክንያት “ጊዜ መራሽ ፍርሃት እንደሸበበው” ያጠየቀበትን አጋጣሚ ለአብነት ማስታወስ ይቻላል።
“የጥበብ ስራ ወይም የምናብ ፈጠራ በፍርሃት ለመሸበብ ሳይሆን ከግዑዙ ዓለም ለመሸሽ ትክክለኛ አማራጭ እና ሁነኛ አቋራጭ መንገድ ነው!” ይላሉ አሜሪካዊ ፀሃፊ ጁሊያ ካሜሩን።
ታዲያ. . . የጥበብን ሃያል ክንድ በውል የተረዳ እና ዘመን በሚሻገሩ ድንቅ የሙዚቃ አልበሞቹ ለትውልዱ የጥበብን ሃያልነት ያስረዳ ጉምቱ ድምፃዊ “አሁን ፈራሁ. . . !” ማለቱ ቆም ብሎ ማሰብ የሚጠይቅ የጋራ የቤት ስራችን ይሆናል።
ጥበብ በጠቢባኑ ፍርሃት ከገበታዋ ላይ እንዳትጎል በትኩረት መላ መሻት የምርጫ ጉዳይ ሊሆን አይገባም።
እንደግለሰብ፥ እንደቤተሰብ፥ እንደማህበረሰብ ብሎም እንደሃገር . . . የህልውናችን ማድመቂያ፤ የተስፋችን ማጠየቂያ እና የጉድለታችን ‘መጠየቂያ የሚሆነው’ ለጥበብ በሰጠነው ትኩረት እና ክብደት ላይ ይንተራሳል።
ለዚህ ትልቅ ጥበባዊ የቤት ስራ አንድም #ምንዳ፤ አንድም #ዕዳ የሆነ የሙዚቃ ቪዲዮ ትኩረቴን ቀይዶ ስለያዘው የግሌን ዕይታ ለማጋራት ወደድኩ።
“ዳርም የለው”. . .
"ዳርም የለው". . . የሙዚቃ ቪዲዮ በአንጋፋው ድምፃዊ አሊ ቢራ እና በወጣቱ ድምፃዊ አብርሃም በላይነህ (ሻላዬ) ውብ ጥምረት ወደ ተደራሲያን ዓይን እና ጆሮ በመካነ~ድር የደረሰው ባሳለፍነው የገና በዓል አመሻሽ ላይ ነበር።
ይህንን ድንቅ የጥበብ አበርክቶ ብዙዎች "ነጠላ ዜማ" ጎራ ውስጥ ሲፈርጁት አስተውያለሁ። በኔ የግል ሙዚቃ አረዳድ ከ"ነጠላ ዜማ" ይልቅ "ድርብ ዜማ" ቢባል በፍፁም የሚያንስበት አይመስለኝም።
[በነገራችን ላይ. . .] ከመደበኛ የነጠላ ዜማ ሸልፍ ለማፈናቀል ሳይሆን፤ ከጥበባዊ ፋይዳ አንፃር ለኋላ እና ለፊተኛው ትውልድ ቅብብሎሽ ተምሳሌታዊ ፅኑ መሸጋገሪያ ድልድይ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል በሚል ቅን መነሻ ነው።
ሁሌም ቢሆን . . . ጥበብ ከተጎናፀፈችው ሃያል ጉልበት አኳያ ታማኝ እና ብርቱ ባለሟሎቿ ህያው ማንፀሪያዎቻችን ናቸው።
የድምፃዊ አሊ እና አብርሃም "ዳርም የለው" የሙዚቃ ቪዲዮ የጥበብን ምድራዊ ስልጣን በጋራ ከፍታውን ያየንበት ድንቅ ስራ ነው።
የ"ዳርም የለው" የሙዚቃ ቪዲዮ መለቀቁን ተከትሎ በርካታ አስተያየቶች በማህበራዊ ሚዲያዎች ሲንሸረሸሩ ታዝበናል።
ለአብነት #ዶ/ር_በድሉ_ዋቅጅራ የጥበብን ባህሪ ከቆዬ ትዝታው ጋር አዋዶ "ዋናው ጉዳይ" ብሎ በአፅንዖት ያሰፈረው አስተያየት ከተነሳሁበት ጭብጥ አኳያ ተመችቶኛል።
". . .ስነ~ጥበብ ምን ዳር አለው? ከህይወትም ይገዝፋል፡፡ ከዘመንም ያልፋል፡፡ ዘላለም ነው፡፡ ተፈጥሮ ያለ ሰው እርቃኗንም ጥበቧ ይበዛል፡፡ ተፈጥሮ ጥበቧን ያኖረችበት አይጠፋትም፡፡ ጥበበኛ ስትሆን ከጥበቧ ትቀይጥህና ዘላለሟ ትሆናለህ፡፡"
በሚል አስተያየቱን አስፍሯል። ዶ/ር #Bedilu_Wakjira ለስነጥበብ ያለውን ጥልቅ መረዳት፣ ብርቱ ስስት እና በድንበር የማይገታው ፋይዳ ከራስ በራው (ፀጉሩ ስለተመለጠ) እስከ የእግሩ አውራ ጥፍር ድረስ በንዝረት ስሜት የተጋባውን ሃሳብ ግሩም አድርጎ ገልፅዋል።
ዕጀ~መንገዴን [ከታላቅ ይቅርታ ጋር] ያልተመቸኝን ሃሳብ በዚሁ ጠቁሜ ማለፍ ወደድኩ። ዶ/ር በድሉ የ"ዳርም የለው" ሙዚቃ ሲሰማ በወጣትነቱ የሚያስታውሳት ሴት ከአሊ ቢራ የሙዚቃ ክዋኔ ጥበብ ብቃት እና ከፍታ ጋር ተጋምዶ የወለደው የትዝታ ስሜት ገፍቶት እንደፃፈ አትቷል።
ለድምፃዊ አሊ ቢራ ያለውንም ጥልቅ አድናቆት እና ዕጅ ንክኪ የፀዳ አክብሮቱን ከሽኖ ገልጦታል። 100% ትክክል፤ 100% ደግሞ ተገቢም ነው።
#ነገር ግን ነፃ ሃሳቡን እንዳሻው የማጋራት ግለሰባዊ መብቱ ቢሆንም፤ የጥበብ #መነፅር አጥልቆ ችሎት ላይ እንደተሰየመ #ዳኛ. . . አንጋፋውን ድምፃዊ አሊ አንስቶ ወጣቱን ድምፃዊ አብርሃም የዘነጋበት አግባብ ፍፁም ርትዑነት ይጎድለዋል።
በስነ~ጥበብ አንባ ውስጥ በዕውቀትም ሆነ በስሜት ከሚመላለስ ትልቅ ባለሟል ተተኪ ወጣቶችን ማበረታታት ይገባል፤ እንደ ዶ/ር በድሉ ካሉ ታላቅ ምሁራን ደግሞ በትክክል ይጠበቃል። [ምናልባት የአሊን ድምፅ ብቻ እየመረጠ አሳልፎ ካላዳመጠው በቀር. . .]
"ዳርም የለው" በሚል ገዢ እሳቤን ራሳችንን እያለማመድን "አንዱን ጥሎ ~ ሌላውን አንጠልጥሎ" በጥበብ ፍኖት መጓዝ እምብዛም ስሜት አይሰጥም።
[ብዙ ጊዜ. . .] #ምሁራን ተጠያቂነታቸው ለህሊናቸው እና ለሚያገለግሉት ማህበረሰብ ነው። #Ring~Side~View ከምሁር የሚጠበቅ ብቻ ሳይሆን የሚገባ ነው።
በሁሉም የሙያ መስክ በአንድ አይን ማየት፤ በአንድ ጆሮ ማዳመጥ ብሎም በአንድ ዕጅ ማጨብጨብ ምሁራዊ ጠባይ ሊሆን አይገባም።
===========
"ዳርም የለዎ ዳርም የለው ላፍታ
የፍቅርሽ . . . . . ሃያሉ. . . ደስታ"
"ዳርም የለው" ~ 'አንድም #ምንዳ፤ አንድም #ዕዳ ነው የሚያስብል ቱባ #ዕይታዎችን ይጋብዛል። የሙዚቃ ቪዲዮው በመካነ~ድር ከተለቀቀ በኋላ ደጋግሜ ስመለከተው እና ሳዳምጠው የፈጠረብኝን ዕይታዎች እንደሚከተለው አኑሬያለሁ።
ዕይታ ~ ፩
~
“ዳርም የለው” ~ በጥምረት ሲያዜሙ ውስጣችን ተቀርፀው የተቀመጡ ያለፈው ትውልድ ድምፃውያንን በምልሰት ያስቴዛል።
[ጥላሁን ገሰሰ እና ብዙነሽ በቀለ፤ ቴዎድሮስ ታደሰ እና የሺመቤት ዱባለ፤ ሂሩት በቀለ እና ታደለ በቀለ . . .ወዘተ “ሁሉም ቢተባበር” በተሰኘ ዘፈን ~ ነዋይ ደበበ ፥ አረጋኸኝ ወራሽ፥ ፀጋዬ እሸቱ በደማቁ ይታወሳሉ።]
የጥምረት የተዜሙት በሙሉ ጥበባዊ ጉልበታቸው እስከዛሬ ከነሙሉ ወዛቸው ዘልቀዋል። #መጣመር በራሱ የጥበብ ወረት በክብር ማቆያ ካዝና እንደሆነ “ዳርም የለው” ዛሬ ላይ ሆነን ወደኋላ በትዝታ የሚመልስ ድንቅ የጥበብ አበርክቶ ነው።
ዕይታ ~ ፪
በኢትዮጵያ ሙዚቃ ኢንዱስትሪ ብዙም ካልተለመዱ ጉዳዮች መካከል የሁለት ወንዶች ቅብብል በአንድ ወጥ ሥራ ውስጥ አለመታየቱ ነው።
ከዚህ አንፃር ከሴትና ወንድ ድምፃውያን ጥምረት ባሻገር ቀደም ባለው ዘመን. . . ምኒልክ ወስናቸው 'ና ግርማ በየነ፣ ጥላሁን ገሰሰ 'ና መሐሙድ አህመድ፥ ማሚላ 'ና ኪቺኒ ጎሳዬ ተስፋዬ 'ና መሐሙድ አህመድ የቀጠለ የሙዚቃ ስራ #ተባዕት ድምፃውያንን አጣምሮ የተከሰተው "ዳርም የለው" መሆኑ የተለየ እይታ ለግሷል።
ዕይታ ~ ፫
ትናትና እና #ነገ የሚጋመዱት #ዛሬ ላይ በተለያዩ ቅርፅ እና ይዘት የተበረከቱ ተሻጋሪ እና አሻጋሪ የጥበብ ትሩፋቶች በትውልዱ ልቦና ሞልተው መፍሰስ ሲችሉ ነው።
በአንጋፋው ድምፃዊ አሊ ቢራ እና በወጣቱ ድምፃዊ አብርሃም በላይነህ (ሻላዬ) በጥምረት ያዜሙበት “ዳርም የለው” የተሰኘው የሙዚቃ ቪዲዮ ዓብይ ማሳያ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።
ከትናንት ትውልድ ድምፃዊ አሊ ቢራን ከዛሬው ትውልድ ወጣቱን ድምፃዊ አብርሃም በላይነህን አጣምሮ መከሰቱ ለነጋችን መሰናሰያ መድረክ ሆኖ ያገለግላል።
የኋላ እና የዛሬ ትውልዶች የጥበብ አበርክቶ የመጪውን ጊዜ ማያያዣ ቀለበት እንደሚሆኑ “ዳርም የለው” የዘርፉ አንቂ ደውል መሆኑን ልብ ይሏል።
ዕይታ ~ ፬
በአሊ ቢራ እና በአብርሃም በላይነህ መካከል ያለው የዕድሜ ልዩነት "የአባት እና የልጅ" በሚባል ደረጃ የሚታይ ነው።
"ዳርም የለው" የሙዚቃ ቪዲዮ የዕድሜ ልዩነታቸውን በጥበብ አቀራርቦ የትውልድን መከባበር ያስነበበ የቃልኪዳን መፅሐፍ ሆና መቅረቡ … የአበርክቶው #ምንዳ ዳር እንደሌለው አስመስክሯል።
አሊ ቢራም የሙያ ልጁን ሳይንቅ፤ አብርሃምም ለሙያ አባቱ በታዛዥነት ስነልቦና ከጉልበቱ ሸብረክ ማለቱ. . . ዳር የሌለው ምስጋና እና አክብሮት ያስቸራቸዋል።
ዕይታ ~ ፭
በዘመናችን በአንጋፋ እና በወጣት ድምፃውያን መካከል ያለው ተጣምሮ እና ተደጋግፎ ያለመስራት አባዜ በ”ዳርም የለው” የሙዚቃ ቪዲዮ ፍፁም ተሰብሯል ለማለት አያስደፍርም። ሳስበው #ዕዳው ገዝፎ ይታየኛል።
“ዳርም የለው” ለሙዚቃ ኢንዱስትሪው ተዋንያን በቀጣይ ያስቀመጠው #ዕዳ እንዳለ ልብ ይሏል። በቀጣይ የቤት ስራ የሰጠ የጥበብ ዕዳ መሆኑን አላምጦ መዋጥ ይጠይቃል።~~~
ታላቅን ማክበር መልካም ነው። ታናሽ ደግሞ መታዘዝን መለማመድ በራሱ መሰልጠን ነው። ለሙዚቃ ዘርፉ ፍፁም ጤና ጤናማ በሆነ አስተሳሰብ ጥበብን ማገልገል ይገባል።
ለማጠናቀቅ ያክል . . . የረዳት ፕሮፌሰር ነቢዩ ባየ ጥበባዊ ምልከታ የሰጠውን አስተያየት ልዋስ። #Nebiyou_Baye
“Power is nothing with out control” የሚል የጎማ ማስታወቂያ ነበር። ለጥበብ በጣም ይሰራል።
የወጣት ጠቢብ ኃይል በበሰለው ተገርቶ እምቅ፣ ሽፍን፣ ምጥን፣ ርግት ያለ የልብ ዜማ ሲያወጣ ይኸን ሙዚቃ ይመስላል።
ወጣቶች በትንሹ ተንጫጭቶ የአድማጭ ጆሮ እና መንፈስ ከማወክ ከትልቅ ውሎ መጣምን በዚህ ልትማሩ ትችላላችሁ።~//~
በ~ዘላለም ሞትባይኖር
ዳር የሌለው ፍቅር አብዝቶ ይስጠን!!