በተስፋዬ ጌትነት
የብልፅግና ፓርቲ ከክልል ክልል ዙረት ፣የጃዋር መሀመድ የዜግነት ጥያቄ ፣የእስክንድር ነጋ ፓርቲ እቅድ ፣የብርሀኑ ነጋ ኢዜማ ፣ የህውሃት ወቅታዊ መግለጫ ፣የጃል መሮ ሸነግ ፣የኦነግ አጀንዳ ፣መጪው ምርጫ ወሬዎች ለጊዜው ደብዝዘው ባለፈው አርብ ኢትዮጵያ ስለገባው ኮሮና ሆኗል የሰሞኑ ኢትዮጵያውያን ጭንቀት ።
ያዘኝ አላዘኝ ፣ነጭ ሽንኩርትና ፌጦ ፣የአፍ ጭንብል ፣ሳሙና ፣እጅ ላይ ያለን ጀርም መግደያ አልኮል… ወዘተ ሆኗል ሰሞኑ ተደጋግመው የሚነሱ ቃላት ። ለባለስልጣኖች ደግሞ ምን አለች? ተብላ ቲዊተር ገፇ በየሰከንዱ የሚታይ በሬድዮ፣ በቴሌቭዥን የምትሰማ ባለተራ መልከ ቀይዋ ዶክተር ሊያ ታደሰ ሆናለች ።
አባቱ ኤርትራዊ ሆነው ባህር ዳር ተወልዶ ያደገው የኢትዮጵያ የውስጥ ፓለቲካ ያልጣመው ዶክተር አሚር አማን በተለይ ከብአዴን ከአሁኑ አዴፓ አመራሮች ግምገማ እና ጭቅጭቅ ሲበዛበት የጤና ሚንስትርነት ስልጣኑን ያውላቹ ብሎ ሀብታሙ ዋረን ቡፌት ጋር ተፃፅፎ የተሻለ ደሞዝ የተሻለ የስራ ድባብ ወደሚያገኝበት አሜሪካ ወደ ሚገኝ አለም አቀፍ ድርጅት አምርቷል ። ሸገር አዲስ ጎማ ቁጠባ በሚገኘው የጤና ሜኒስቴር የአሚር ምክትል የነበረቸው አዲስ አበባ ተወልዳ ያደገችው የቀድሞዋ የምስኪሀዙናን ተማሪ ዶክተር ሊያ ታደሰ ሚኒስትር አርገው ጠ/ ሚኒስቴር ዶክተር አብይ በሾሟት ማግሰት ኢትዮጵያ ስትሰጋ የነበረው ከቻይን ውሀን ተነስቶ 154 ሀገራት ላይ ገብቶ 6,000 በላይ ሰው ሒወትን የቀጠፈው ከለሊት ወፍ ወደ ሰው የተላለፈው የኮሮና ቫይረስ ኢትዮጵያ ውስጥ ከቡርኪና ፋሶ በመጣ ጃፓናዊ በኩል ለመጀመርያ ጊዜ ገባ ።
ድንጋጤ ፣ስጋትና ፍርሀት በድህነት የሚንገላታውን ህዝብ ተቀበለው። ሚኒስትር ሆና ከመሾሟ በፊት ሚኒስትር ዴኤታ ሆና በሽታው እንዳይገባ መረጃ ታደርስ የነበረችው ፍልቅልቂቷ የጅማ ህክምና ምሩቅ ዶክተር ሊያ ታደሰ ቫይረሱ ገባ በተባለ በአራተኛ ቀን ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ ሰዎች ከበዙበት ቦታ መቆጠብን ፣እጅን በሳሙና መታጠብን እንደ አማራጭ አድርጋ ስርጭቱን ለመግታት ያደረገችው ጥረት እጅግ የሚደነቅ ነው ።
ነገር ግን ኢትዮጵያ የገባው ጃፓናው ተመርምሮ ውጤቱ ማታ ታውቆ ወዲያው ለህብተረሰቡ አሳውቃ አስፈላጊው ጥንቃቄ ህብረተሰቡ ማድረግ ሲችል ከ10 ሰአት በላይ ዘግይታ ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠቷ ትችትን አስከትሎቧታል ።
በቫይረሱ ተይዘዋል ከተባሉ ሰዎች ጋር ንክኪ የነበራቸው መንግስት በክትትል ያልደረሰባቸው ሰዎች በ10 ሰአት ውስጥ ከብዙ ሰዎች ጋር ይነካካሉ ።ይሄም የቫይረሱ ስርጭትን ለመግታት አሉታዊ ተፅእኖ ይኖረዋል። እንደውም የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ስራቸው ባይሆንም ቀድመው ከሚኒስትሯ በፊት ቫይረሱ ኢትዮጵያ እንደገባ መናገራቸው ሰው ቀድሞ እንዲጠነቅቅ በማድረግ ረገድ አስተዋፆ አድርገዋል።
በሚኒስትር ማእረግ ከተሾመች 15 ቀን ያልሞላት ዶክተር ሊያ በሽታውን ሰርጭት ለማቆም ልክ እንደ አውሮፓ የጤና ሚኒስትሮች ይሄን አርጉ በማለት ቀጭን ትእዛዝ መስጠት ይከብዳታል ።ለምሳሌ የበሽታው ስርጭት አየባሰ ቢመጣ ከቤታቹ አትውጡ ብትል ካልሰራ መብላት የማይችለው አብዛኛው ማህበረሰብ የሚበላ ከየት ያመጣል? መንግስት ህዝቡን ለአንድ ወር ከቤት አትውጣ ቢለው ከ110 ሚልየን ህዝብ ስንቱ ነው የአንድ ወር ቀለብ በራሱ መብላት የሚችለው? የቤት ኪራይ ማን ይከፍልለታል? ስራ እየሰራ እንኳን ኑሮ ወድነት ያንገሸገሸው ከ80% በላይ የሆነው ህዝብ ስራ አቁም! ቫይረሱ እንዳይሰራጭ ቢባል ምን በልቼ ብሎ መጠየቁ አይቀርም ።
ለቫይረሱ መከላከያ 300 ሚልየን ብር ( በነፍስ ወከፍ ሲሰላ 2 ብር ከሰባ ሳንቲም)የመደበው መንግስት መንግስት ህዝቡን አንድ ወር መመገብ ይችላል የሚለው እራሱ ለአዲሷ ሚኒስትር ራስ ምታት የሆነ ነገር ነው ።
ከሁለት ነጥብ ስድስት ቢልየን ዶላር ያነሰ አመታዊ የውጭ ንግድ ይዞ አስር ሚልየን ስራ አጥ ወጣት አቅፎ ኢኮኖሚያው ጫና ያለው የኮሮና ስርጭት መግቻ መፍትሄ ማቅረብ ምን አልባት ቤቱ በርሀብ የሚሞት ሰው ሊያስመለክት ይችላል።
ዶክተሯ ከቻይና የተነሳውን የኮሮና ቫይረስ ወደ ሀገር እንዳይመጣ ወደ ሀገር ወደ ኢትዮጵያ የሚደረገውን በረራ ማስቆም አለባት ሲሉ በዙዎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል ነገር ግን ይሄ ነገር ለመወሰን ለሚኒስትሯ የምድር ወገብን በእግር የሟቋረጥን ያክል ከባድ ነው።
።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አመታው ገቢው የሀገሪቷን 40% አመታ ዊ በጀት ድረስ ሲደርስ ከዚህ ገቢው ደግሞ ትልቁን ገንዘብ የሚያገኘው ቻይና እና ምእራብ አፍሪቃ እየበረረ ነው ።ሚኒስትሯ ይሄን በረራ ብታስቆም የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለመደገፍ ሌላ ምን አማራጭ አለ ? ብሎ መጠየቅ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው ።
8 ሚልየን ህዝቧ ስንዴ እየተረዳባት ላለች ሀገር ፣የብሔር ፓለቲካ የቀሰቀሰው ግጭት ኢኮኖሚዋን ላቀዘቀዘው የምስራቅ አፍሪካዊቷ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ስራ ቢያቆም በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ነው ነው ሚሆንባት ። ለኮሮና ቫይረስ የፊት ማስክ ለሁሉም ህዝቧ ማዳረስ አቅም የሌላት ሀገር የአየር መንገድ ገቢ ቢቀር ምን ልትሆን ትችላለች? ብሎ ማሰብም ተገቢ ነው ።
ከሰው ነፍስ አይበልጥም ከተባለ መንግስት ሰው እቤቱ ቢቀመጥ የማብላት አቅም አለው ወይ ብሎም ማሰብ ይፈልጋል።
ሌላው ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ የዶክተሯ እንቅፋት እየሆነ ያለው ነገር ህብረተሰቡ ያለው የተዛባ መረጃ ነው ።ትላልቅ ሚድያዎች ሳይቀሩ የተዛባ መረጃ ሲያስተላልፉ ይስተዋላሉ ። ዶክተሯ ከንክኪ ፣ከመጨባበጥ ተቆጠቡ ብትልም መንገድ ላይ ከተወሰኑት ሰዎች በቀር ህብረተሰቡ አየተጠነቀቀ አይደለም።በመንገድ ላይ ፣በታክሲ ላት ታጭቆ የሚሄደው ሰው ለአጀብ ነው ።በመመገቢያ ስፍራዎች ሳይቀር ሰዎች በተጨናነቀ የምግብ ስፍራ ሲመገቡ ተስተውለዋል ።ይሄ ሁኔታ ከጣልያን ከተከሰተው ነገር ጋር ያመሳስለዋል። በጣልያን ኮሮና ገባ ጥንቃቄ አርጉ ተብሎ ሲነገር የሰዎች የእለት እለት እንቅስቃሴ እንደተለመደው ነበር ።በሶስት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ከ2,000 በላይ ሰው ሲሞት ግን ሰው ቤት መዋል ጀመረ ።መንገዶች ተዘጉ ።እንቅስቃሴ ቆመ።
ይሄን ነገር ዶክተር ሊያ ሀገራቸው ላይ እንዳይሆን “ሳይቃጠል በቅጠል ” ብለው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀናጅተው የጀመሩትን ስራ ጥበብ በተሞላበት መንገድ ማስቀጠል ይኖርባቸዋል ።ኮሮናን ለመዋጋት ግሪክ ና እስራኤል እንደጀመሩት ማንኛውም ኢትዮጵያ የሚገባ ሰው ቢያንስ ለ14 ቀን ተለይቶ ተቀምጦ ቫይረሱ እንደሌለበት ተረጋግጦ መግባት ይኖርበታል።
የ48 አመቱ ጃፓናዊ ለ14 ቀን ተለይቶ ተቀምጦ ቢሆን ኖሮ ቫይረሱ ወደ ሀገራችን ባልገባ ነበር ።
በተረፈ የቫይረሱን ስርጭት አየባሰ ቢሄድ ምን ኢኮኖሚያዊና ህብተረሰባዊ ጤናዊ ውሳኔዎችን ከአሁኑ ቁጭ ብሎ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ማዘጋጀት የዶክተር ሊያ ትልቁ የቤት ስራ ይሆናል ። ኮሮና ከተስፋፋ መጪው ምርጫን ከማሰረዝ አንስቶ የህዳሴ ግድብንና ሌሎች የሀገሪቱን ትላልቅ ፕሮጀከቶችን የማስቆም እና ከፍተኛ ስራ የሌለው ማህብረሰብ ፈጥሮ ምግብ የሚቸገር ሰው በሚልየኖች ይፈጥራል ።ይሄ ደግሞ ዝርፍያን ጨምሮ አደገኛ ማህበረሰባው ቀውስ ይፈጥራል ። የዚህ ድምር በቋፍ የቆመውን ፓለቲካው ችግር ወደ ከፍ አለ ግጭት አለበት ሀገር ይወስደዋል ።