ኢትዮጵያ ውስጥ ኮሮና ቫይረስ የተገኘበት ጃፓናዊ በኩሪፍቱ ሪዞርት” ከእኔ ጋር ያደረች ሴት” የለም ብሏል



ባለፈው ሳምንት በምርመራ ኢትዮጵያ ውሰጥ ኮሮና ቫይረስ የተገኘበት ጃፓናው አዳማ / ናዝሬት በሚገኘው ኩሪፍቱ ሪዞርት አብራው እንዲት ሴት እንዳደረችና እንደጠፋች በማህበራዊ ሚዲያ የተወራው ነገር ፈፅሞ ውሸት ነው ብሏል ።

በኢትዮጵያ የሚገኘው የጃፓን ዓለም አቀፍ የትብብር ኤጀንሲ ለፊደል ፖስት እንደገለፀው ባለትዳሩ ጃፓናዊ በዚህ ጉዳይ ላይ ኤጀንሲው ከአንዲት ኢትዮጵያው ሴት ጋር በሪዞርቱ ክፍል ውስጥ አድርሀል ወይ? ተብሎ ለተጠየቀው ጥያቄ ሲመልስ ” 100 ፐርሰንት ውሸት ብቻዬን ነው ያደርኩት “በማለት መልሷል።
በጉዳዩ ላይ ፊደል ፓስት የኩሩፍቱ ሆቴል ባለቤትን አቶ ታዲዮስ በለጠን ጠይቆ የነበረ ሲሆን ዛሬ ከዱባይ እንደመጡና በጉዳዩ ላይ ምንም መረጃ እንደሌላቸው ተናግረዋል ።
የአዳማ ኩሪፍቱ ሪዞርተ አስተዳደር ሀላፊ የሆኑት አቶ ኪሩቤል ሰብስቤ ከተደጋጋሚ ስልክ ጥሪ በኋላ ይሄን ምላሽ ሰጥተዋል ።
” ሰውዬው እዚህ ይደር አይደር ምናውቀው ነገር የለም ።ይሄን ጉዳይ ጤና ቢሮ ሄዳቹ ጠይቁ “ብለዋል ።

በኦሮሚያ ጤና ቢሮ ህብረተሰብ ጤና ምርምር ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ገመቹ ሹሜ ግን ጉዳዮን ቢሮው እየመረመረ መሆኑን ተናግረዋል።
” ጃፖናዊው ከሴት ጋር አድሮ ነበረ ።እሷም ጠፍታለች የሚለው ዜና እኛም በወሬ ደረጃ ደርሶን ነበር ።እውነት ለመናገር በተጨባጭ ያገኘነው ነገር የለም ።አሁንም ነገሩን አየመረመርን ነው ።አዲስ ነገር ካለ ለህዝባችን የምናሳውቅ ይሆናል” ብለዋል።

 የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የህዝብ ግንኙነት ክፍል ሰራተኛ አቶ መላኩ አበበ በበኩላቸው ከሰውዬው ጋር ንኪኪ አላቸው የተባሉ ሰዎች ሁላ ወደ ለይቶ ማቆያ ክፍል መወሰዳቸውን ተናግረዋል።
” ሰውዬው ከማን ጋር ነው ያደረው ወይንም ብቻውን ያደረው? በሚለው ጉዳይ ላይ አስተያየት መስጠት ይከብደኛል ።የግለሰብ ጉዳይ ስለሆነ ።እኛ ግን ከሰውዬ ጋር ንከኪ አላቸው ብለን የጠረጠርናቸውን ሰዎች ሁላ ወደ መለያ ክፍል አስገብተን ክትትልና ምርመራ አርገናል ።አብዛኞቹም የቫይረሱ ምልክት ስላልተገኘባቸው ወደ ቤታቸው ተመልሰዋል ። ከጃፓኑ ጋር አድራ ያመለጠች ሴት አለ ስለተባለው ነገር አስከአሁን የደረሰን ሪፖርት የለም ” ብለዋል ።
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ጄላን መሀመድ በበኩላቸው በወሬ ደረጃ ጉዳዩን እንደሰሙት ገልፀው ነገሩ በተመለከተ ከየትኛውም ፖሊስ ጣቢያ ሪፖርት እንዳልመጣ ተናግረዋል።
ከጃፖን ቡሪካና ፋሶ ከዛም ወደ ኢትዮጵያ የመጣው የ44 አመቱ ጃፓናዊ የትምህርት ባለሙያ ሲሆን የጃፓን ዓለም አቀፍ የትብብር ኤጀንሲ ትምህርት ቤቶች ላይ ድጋፍ ለሚያደርገው የሒሳብና የሳይንስ ትምህርቶች ላይ ምክክር ለማድረግ ነበር ወደ አዳማ እና አሰላ የተንቀሳቀሰው። ባለሙያው በአሁኑ ሰአት በጥሩ ጤንነት ላይ እንደሚገኝ ለፊደል ፖስት የደረሰው መረጃ ያሳያል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *