በአየር መንገድ እየተፈፀመ ያለው የሰራተኞች በደል ምንድን ነው? አቶ ማርቆስ የሱወርቅ ይነግረናል




“በኮሮናቫይረስ ምክንያት አየር መንገዱ ሰራተኞቹን ፍቃድ ማስወጣቱ ትክክል ነው ነገር ግን በመቶዎች የሚቆጠሩ “ኮንትራት” ሰራተኞች ፣የበረራ አስተናጋጆች፣ የትኬት ሰራተኞች ፣ ቴክኒሽያኖች እና የምግብ ዝግጅት ሰራተኞችን ጨምሮ ያለ ክፍያ የ 90 ቀናት እረፍት እንዲወጡ ተደርገዋል። አየር መንገዱ የሰራተኛ ማህበራችን እንደልቡ አንዳይንቀሳቀስ እንቅፋት ሆኗል ።የማህበራችን ሊቀመንበር አባሯል።ህግና ስርአት በሌለው መልኩ ብዙ ነገሮች አየተከናወኑ ነው” ሲልየአውሮፕላን ቴክኒሺያኑ እና የኢትዮጵያ አየርመንገድ ግሩፕ ሰራተኞች ማህበር ም/ትል ሊቀመንበር አቶ ማርቆስ የሱወርቅ ያስረዳል።
ፊደል ፖስት ዋና አዘጋጅ ተስፋዬ ጌትነት አቶ ማርቆስን በአየር መንገድ ሰራተኞች የወቅቱ ስጋት ላይና በአጠቃላይ የማህበራቸው ፈተና ላይ አወርቶታል ።ቃለ መጠየቁ በአጭሩ ከታች ያለውን ይመስላል;

ፊደል ፖስት፡ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ ሁለት የሰራተኛ ማህበር አለ ይሄ የሆነበት ምክንያት ምንድን ነው?

ማርቆስ የሱወርቅ: እንግዲህ ምንም ለመግለፅ እንኳን ረዘም ያለ ሂደት ቢሆንም፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት በአዋጅ ተዋህደው “የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩኘ” ተብለው ተጠሩ። ታዲያ እነዚህ ሁለት ተቋማት ተዋህደው አንድ ተቋም መፍጠራቸውን ተከትሎ በሁለቱ ተቋማት ውስጥ የሚገኙትን ሁለት የሰራተኛ ማህበራት ማዋሀድ አስፈላጊ ሆኖ ተገኘ። እነዚህንም ማህበራት ለማዋሀድ ወደ ሁለት አመታት ገደማ የሚሆን ውይይት በማህበራቱ መሪዎች እና በሌሎች አካላት በኩል ተካሒዷል። ከእነዚህ ብዙ ውይይቶች በኋላ ማህበራቱ ጠቅላላ ጉባኤያቸውን በመጥራት ራሳቸውን አክስመው ወደ አንድ ውህድ ማህበር እንዲመጡ ተወስኖ ስብሰባው ግንቦት 1,2011 ቀን እንዲደረግ ተወሰነ። እንግዲህ እኔን ጨምሮ ብዙ የአየር መንገዱ ሰራተኛ፤ የነበረው ማህበር “ጠንካራ አይደለም፣ መብቴን ሊያስከብር አይችልም” የሚል እሳቤ ስለነበረን በዚህ የውህደት ምርጫ ላይ ከውህደቱ በኋላ የሚፈጠረውን አዲስ ማህበር ጠንካራ እና የሰራተኞችን መብት ማስከበር የሚችል ለማድረግ ሰራተኛው በጠቅላላ ጉባኤው ላይ ተገኝቶ ድምፁን እንዲሰጥ ከፍተኛ ቅስቀሳ አደረግን። ግንቦት 1,2011 ላይ ከዚህ በፊት በሰራተኛ ማህበር ስብሰባ ባልተለመደ መልኩ ብዛት ያለው ሰው ተገኝቶ ምርጫ አደረግን። ሰራተኛውም እኛን መርጦ ጠንካራ ማህበር መመስረቱን አምኖ ወደየቤቱ ሔደ።

ይህ ምርጫ ግን እንከን ገጠመው። ምን ማለቴ ነው ፤ በዋናነት አስተዳደሩ “ዋና አብራሪዎች (ካፒቴኖች) የስራ መሪዎች ስለሆነ የሰራተኛ ማህበር ውስጥ የመሳተፍ መብት የላቸውም” የሚል ቅሬታ ለሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር አቀረበ። ይሕንንም ለመፍታት የ ኢ.ሰ.ማ.ኮ እና የትራንስፖርት እና መገናኛ ሰራተኞች ማህበራት ኮንፌደሬሽን መሪዎች አምስት ወራት የፈጀ ድርድር ከአስተዳደሩ ጋር አድርገዋል። አደራዳሪውም ሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር መስሪያ ቤት ነበር።
በእነዚህ አምስት ወራት ውስጥ ከዚህ ድርድር ባሻገር የተፈጠሩ ነገሮች ነበሩ። ለምሳሌ፤ ተመራጭ የነበረው ካፒቴን የሽዋስ ፈንታሁን ወደ ቻድ ሔዶ ስራ መስራት እንዳለበት ተገዷል። እኔ ለ ሁለት ወራት ገደማ ከስራ ታግጄ ነበር ፣ በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ የነበሩ ሰራተኞች የተለያየ ነገር ደርሶባቸዋል።

እንግዲህ በመጨረሻ ዋና አብራሪዎች የስራ መሪዎች አይደሉም ስለዚህ በሰራተኛ ማህበር መደራጀት ይችላሉ የሚለው ከተወሰነ በኋላ፤ ዳግም የሰራተኛ ማህበሩ መሪዎች ምርጫ መስከረም 10 ቀን 2012 ዓ.ም እንዲደረግ ተወሰነ። ስብሰባውንም የጠራው ኢ.ሰ.ማ.ኮ ነው ምክንያቱም በዚህ ወቅት ሰራተኛውን ስብሰባ ለመጥራት መብት ያለው ህጋዊ ማህበር አልነበረም። ሁለቱም ማህበራት የስራ ግዜያቸው አብቅቷል። ይሕ ምርጫ ሲጠራ ወዲያውኑ የአየር መንገዱ አስተዳደር ለሰራተኞች በሙሉ “ህገወጥ ስብሰባን ይመለከታል” የሚል መልእክት በማስተላለፍ ሰራተኞች ስብሰባውን እንዳይሔዱ አስጠነቀቀ። በድጋሚ ከጥቂት ቀናት በኋላ ደግሞ ስብሰባው ድርጅቱ ግቢ ውስጥ እንደሚደረግ መልእክት አስተላለፈ።
የሆነው ሆኖ ምርጫው ህጋዊ ሒደቱን ተከትሎ ተካሔደ ። ሁለት ማህበራትን በማዋሀድ የተገኘው አዲሱ ውሕድ ማህበራችንም ካፒቴን የሺዋስ ፈንታሁንን ሊቀመንበር እኔን ደግሞ ምክትል ሊቀመንበር አድርጎ መስከረም 10 ቀን 2012 ዓ.ም ተመሰረተ ማለት ነው።

ይሕ ከሆነ በኋላ የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኛ ማህበር መሪዎች ማለትም አዋህደን አዲስ ማህበር የመሰረትንበት ማህበር፤ እና አስተዳደሩ ለሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር በጭብጡ የተመሰረተው ማህበር ተቀባይነት የለውም ፈቃድ እንዳይሰጠው የሚል ቅሬታ አሰሙ ። አስተዳደሩ ይባስ ብሎ “ፈቃድ ቢሰጠው እንኳ አብሬ አልሰራም” ብሎ ለሚኒስትር መስሪያ ቤቱ አሳወቀ።

እንግዲህ ይሕ ከተፈጠረ በኋላ የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኛ ማህበር መሪዎች መስከረም 24 ቀን ከቀኑ 5 ሰአት ስብሰባ ጠርተው፤ በዚያው ቀን ከቀኑ 8:00 ሰአት 59 ሰው የተገኘበት ምርጫ አደረጉ። ከዚያም የቀድሞውን ማህበር አስቀጠልነው የሚል ትርክት ይዘው ሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አመለከቱ። ታዲያ በውህደት የተገኘው የእኛ ማህበር ከአዲስ ማህበር፤ ሁለተኛው ማህበር ደግሞ የቀድሞው ተባሉ ማለት ነው።

ለእኛ ማህበር በ ጥቅምት 11, 2012 ዓ.ም “የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩኘ መሰረታዊ የሰራተኛ ማህበር” ተብሎ ፈቃድ ከተሰጠ በኋላ፤ እስከ አሁን ድረስ እና ሁልግዜ ባሰብነው ግዜ ግራ በሚያጋባን አይነት ሁኔታ ለሁለተኛው ማህበር “የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩኘ ቀዳማዊ መሰረታዊ የሰራተኛ ማህበር” ተብሎ ፈቃድ ተሰጠ።

ሳልጠቅሰው ማለፍ የማልፈልገው ይሕ ማህበር ማለት እኛ አባል የነበርንበት እና አዋህደን ወደ አዲስ ያመጣነው ማህበር ነው። እንግዲህ ይሕ ማለት ማህበሩ የአባላት ቁጥር ብሎ የሚናገረው ቁጥር የእኛንም አባላት ጭምር የያዘ ቁጥር ነው።

ያም ሆኖ እስካሁን ድረስ አብዛኛውን የአባላት ቁጥር የያዘው ማህበር የትኛው እንደሆነ የሚያሳይ በሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ የተሰጠ ማረጋገጫ የለም።ይሕ ስልጣን ያለውም ሚኒስትር መ/ቤቱ ብቻ ነው።



ፊደል ፖስት፡ ማህበራቹ ከተመሰረተ ጀምሮ በዋነኝነት የሰራቹትን ስራ ብትነግሩን ?

ማርቆስ የሱወርቅ: ማህበራችን ከሰራቸው ስራዎች የመጀመሪያ ብለን ልንጠቅሰው የምንችለው ፤ ሰራተኛው ስለጠንካራ የሰራተኛ ማህበር ጥቅም እና አስፈላጊነት ያለውን መረዳት መጨመር ነው። ከዚህ አንፃር በከፊል ተሳክቶልናል ብለን እናምናለን። ምክንያቱም ሰራተኛው ከፊቱ የተሻለ አሁን የመደራጀትን አስፈላጊነት ተረድቷል።

ሌላው እስካሁን በአስተዳደሩ ይደረጉ የነበሩ ህገወጥ አሰራሮች እንዲሁም ህግን መሰረት አላደረጉም ብለን የምናምናቸውን ፖሊሲዎች ከማስቀረት አንፃር ስራዎችን እየሰራን ነው።
በ ፍርድ ቤት የተያዙ እና ገና ወደ ፍርድ ቤት የምንወስዳቸው የሰራተኛው ጉዳዮች አሉ።

የሰራተኛውን ነፃነት እና የመደራጀት መብት ከማስከበር አንፃር ብዙ ስራዎችን በመስራትም ላይ እንገኛለን። በዚህ ውስጥ ደግም ማህበራችን አባል የሆነባቸው ኢ.ሰ.ማ.ኮ ፣ የ ትራንስፖርት እና መገናኛ ሰራተኛ ማህበራት ኢንዱስትሪ ፌደሬሽን እንዲሁም ዓለም ዓቀፍ ተቋማት ከጎናችን ናቸው ያንን ሳናመሰግን አናልፍም።

ከዚህ ባለፈ ግን፤ አስተዳደሩ እስካሁን በተረዳነው ልክ ማህበራችንን ከማጥቃት እና ከማግለል ባለፈ ምንም የመደራደር ወይም የመወያየት ፍላጎት ባለማሳየቱ ህገወጥ የሆኑ ውይይቶች ተግባራትን በሙሉ በፍርድ ሒደት መፍትሔ እያሰጠን እንጂ በመወያየት ያደረግናቸው ነገሮች የሉም። ያም ቢሆን ማህበራችን ህግን መሰረት ያደረጉ ለኢንዱስትሪው ሰላም ጠቃሚ ናቸው ብሎ ያምናል።



ፊደል ፖስት: ማህበራችሁ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ጋር በመሰረታዊነት ያለው ቅራኔ ምንድን ነው?

ማርቆስ የሱወርቅ: አስተዳደሩ ማህበራችን ከተመሰረተ ጀምሮ በማህበር እንቅስቃሴ ውስጥ ከፍተኛ ጣልቃ ገብነት ሲያሳይ ነበር። ከዚያም በኋላ በምናደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ለምን እንደሆነ ባይገባንም በጥላቻ እና በጠላትነት አይን እንደሚመለከተን ተረድተናል።

ለሰራተኞች የመደራጀት መብት ወሳኝ ቢሆንም አስተዳደሩ ማህበራችን ላይ ይሕንን መብት እንዳንተገብር ጫና አድርጓል። ለምሳሌ የአባላት ምዝገባ በድርጅቱ ግቢ ውስጥ ልናደርግ አንችልም።
በአዋጅ በተቀመጠው መሰረት ድርጅቱ የአባላትን መዋጮ ከአባላት ደሞዝ ቆርጦ ወደማህበራችን ሒሳብ የማስገባት ግዴታ ቢኖርበትም ይሕንን እየተወጣ አይደለም። በዚህም ምክንያት ክስ መስርተን የፍርድ ቤት ትእዛዝ ወጥቶ አስተዳደሩ እንዲፈፅመው ቢታዘዝም እስካሁን ይሕንን አላደረገም። በትንሹ እንኳ አስተዳደሩ የምንፅፈውን ደብዳቤ ለመቀበል ፈቃደኛ አይደለም።

እነዚህ ጥቂቶቹ ሲሆኑ በአጠቃላይ እንደማህበር አስተዳደሩ የመደራጀት መብት ላይ በሚያደርገው ጫና እና በሰራተኛ ማህበር እንቅስቃሴ ላይ በሚያደርገው ጣልቃ ገብነት ከፍተኛ ቅራኔ ተፈጥሯል። ይሕንንም ተከትሎ ከ ኢ.ሰ.ማ.ኮ ጀምሮ እስከ “International Transport Federation” (ITF) እና “International Confederation of Trade Unions-Africa” ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በፃፉት ደብዳቤ በአስተዳደሩ እየተፈፀመ ያለውን ህገወጥ ጣልቃ ገብነት ጣልቃ ገብተው እንዲያስቆሙ ጠይቀዋል።

ነገር ግን ይባስ ብሎ ፤ የማህበራችን ሊቀመንበር ካፒቴን የሺዋስ ፈንታሁን ለ 6 ወራት ከስራ ውጪ ሆኖ ያለደሞዝ ከቆየ በኋላ ፤ ጉዳዩ በፍርድቤት ውሳኔ እየጠበቀ ያለ ጉዳይ ሆኖ እያለ ከጥቂት ቀናት በፊት ህገወጥ በሆነ መልኩ ከስራ ተሰናብቷል። ይሕ ተቀባይነት የሌለውና በማህበራችን ላይ የተቃጣ ጥቃት ነው ብለን እናምናለን።

ፊደል ፖስት: በአየር መንገዱ ውስጥ አሉ ከምትሏቸው የሰራተኞች በደል ውስጥ ዋና ዋናዎቹን ሊነግሩን ይችላሉ?

ማርቆስ የሱወርቅ: እንግዲህ ላለፉት ጥቂት ዓመታት ጠንካራ እና ለሰራተኛው መቆም የሚችል ሰራተኛ አልነበረም ብለን በማመናችን ስር የሰደዱ በደሎች እንደሚኖሩ ግልፅ ነው።

በአጠቃላይ ሲታይ እንደማህበር አሁን ለመዘርዘር የሚከብዱ ብዙ በደሎች እንዳሉ እናውቃለን።

ነገር ግን በፖሊሲ ደረጃ ተፅፈው ካሉት እንኳ ብንጠቅስ ፤ አንድ ሰራተኛ የስራ ልምድ ሊሰጠው የሚችለው ከድርጅቱ ጋር ያለው የስራ ውል ሲቋረጥ ብቻ ነው።ይሕ ከአሰሪ እና ሰራተኛ አዋጁ አንፃር ተቀባይነት የለውም።
የብዙ ኮንትራት ሰራተኞች ቅጥር ህግን መሰረት ያደረገ አለመሆኑ ሌላው ከአዋጁ ጋር የሚጣረስ አሰራር ነው። በኮንትራት ለዓመታት በአየር መንገዱ ውስጥ የሚሰሩ በርካታ ሰራተኞች አሉ።

እነዚህን እንደ ምሳሌ ጠቀስኩ እንጂ በአይነት የብዙ አይነት የሰራተኛ በደሎች እና የመብት ጥሰቶች እንዳሉ እናውቃለን።




ፊደል ፖስት: የአየር መንገድ ሰራተኞች ቤት ለመስራት መኪናም ለመግዛት ብድር ሲቸገሩ ይታያሉ ይህን ለመቅረፍ የጀመራቹት ነገር ካለ ቢገለፅ?

ማርቆስ የሱወርቅ: አሁን በማህበራችን ውስጥ በስራ አስፈፃሚነት የሚገኙ ግለሰቦች ሊቀ መንበራችንን ጨምሮ ከ ሁለት ዓመት በፊት የጀመሩት ስራ በጥቂቱ ፍሬ አፍርቶ ድርጅቱ ከ ኢትዮጲያ ንግድ ባንክ ጋር ባደረገው ስምምነት አሁን ሰራተኞች ብድር እንዲያገኙ ሆኗል።

ነገር ግን ይሕ ብድር ከፍተኛ ገቢ ያላቸውን ሰራተኞች እንጂ መካከለኛ እና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ሰራተኞች ተጠቃሚ የሚያደርግ አይነት አይደለም። የወለድ መጠኑ እምብዛም አዋጭ የሚባል አይደለም።

በአሁኑ ሰአት ግን ለሰራተኞች ብድር ሌላ እየሰራን ያለነው ስራ የለም። የሰራተኞች መሰረታዊ መብቶች ሲከበሩ ግን ከዚያ በኋላ ብዙ ለመስራት የምናቅዳቸው ሰራተኛውን በሚገባ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎች አሉ።

ፊደል ፖስት: ከኮሮና ቫይረስ ጋር ተያይዞ አየር መንገዱ የወሰደውን የብዙ በረራዎች መሰረዝና ሰራተኞችና ፍቃድ እንዲወጡ ማድረግ እርምጃ እንዴት ታዩታላቹ?

ማርቆስ የሱወርቅ: አየር መንገዱ ብዙ በረራዎችን መሰረዙ ትክክለኛ እርምጃ ነው።
የሰራተኞች እረፍት እንዲወጡ መደረግም ቢሆን የአየር መንገዱ ስራ ከመቀዛቀዙም አንፃር ሆነ ማህበራዊ ፈቀቅታን ከመጠበቅ አንፃር ትክክለኛ ውሳኔ ነው።

ነገር ግን፤ አሁን ባለው ሁኔታ በመቶዎች የሚቆጠሩ “ኮንትራት” ሰራተኞች ፣የበረራ አስተናጋጆች፣ የትኬት ሰራተኞች ፣ ቴክኒሽያኖች እና የምግብ ዝግጅት ሰራተኞችን ጨምሮ ያለ ክፍያ የ 90 ቀናት እረፍት እንዲወጡ ተደርገዋል። ይሕ አግባብ ነው ብለን አናምንም። ጊዜውን ያልጠበቀ እና ወቅታዊ የሀገሪቱን ሁኔታ ያለገናዘበ ከመሆኑም ባሻገር ፤ መንግስት በወረርሽኙ ሊመጣ የሚችለውን ማህበራዊ ቀውስ ለመከላከል አቅዶ ያወጣውን መመሪያ ያልተከተለ ነው። በድርጅቱ ውስጥ በውጭ ምንዛሬ ከፍተኛ ደሞዝ የሚከፈላቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ የኮንትራት ተቀጣሪ አበራሪዎች እያሉ ያነሰ ደሞዝ የሚከፈላቸው ኢትዮጵያውያንን ያለ ደሞዝ እረፍት ማስወጣት በሞራልም ቢሆን ተቀባይነት የለውም።

በአሁን ሰአት ማንኛውም በሰራተኛው ላይ የሚወሰዱ እርምጃዎች መቃኘት ያለባቸው ድርጅትን ከማቆየት አንፃር እንጂ ከትርፍ አንፃር ሊሆን አይገባውም። ስለዚህ ድርጅትን ለማቆየት ሲባል የሰራተኞችን ደሞዝ ለጊዜውም ቢሆን ማቆም የሚል ደረጃ ላይ ደርሰናል ወይ? ደርሰናል ብለን አናስብም። ወደፊት ከደረስንም ግን ፤ ፍትሀዊ በሆነ መንገድ መሆን ይገባዋል እንላለን።

ፊደል ፖስት: ከኮሮና ቫይረስ ጋር ተያይዞ አየር መንገዱ ቋሚ ሰራተኞችን አልቀነስኩም ብሎ በሀሰትም ስሜ እየጠፋ ነው ይላል የእናንተ ምላሽ ምንድን ነው?

ማርቆስ የሱወርቅ: በመጀመሪያ ማህበራችን ምንም አይነት በሀሰት ስም የማጥፋት ዓላማ የሌለው ለእውነት እና ለፍትህ ብቻ የቆመ ማህበር መሆኑን ማረጋገጥ እንፈልጋለን።

እንግዲህ የጠቀስክልኝ ይሕ የአስተዳደሩ መልስ አሳሳች ነው። ምክንያቱም እኛ እያልን ያለነው ፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ የኮንትራት ሰራተኞች ማለትም የበረራ አስተናጋጆች፣ የማርኬቲንግ ሰራተኞች፣ ቴክኒሽያኖች ፣ የ ኬተሪንግ ሰራተኞች እና ሌሎች ያለ ደሞዝ እረፍት እንዲወጡ ተደርገዋል ነው። አስተዳደሩ ቋሚ ሰራተኛ አልቀነስኩም ማለቱ ትክክል ነው። ነገር ግን እኛ እያነሳን ካለነው ጥያቄ ጋር ግንኙነት የለውም። አንድ መታወቅ ያለበት ነገር ግን አንድ ሰራተኛ ቋሚም ሆነ ኮንትራት በገቢ መቋረጥ የሚደርስበት ኢኮኖሚያዊ ጉዳት የቅጥር ሁኔታው ላይ የተመሰረተ አለመሆኑ ነው።

በመሰረቱ እነዚህ ሰራተኞች በአስተዳደሩ አጠራር “ኮንትራት” ተባሉ እንጂ የቅጥር ሒደቱ እና የሰሩበት ግዜ በህግ ፊት ቋሚ ሰራተኞች የሚያደርጋቸው ነው። ለዚያም ነው ማሕበራችን እንደ ቋሚ ሰራተኞች የሚቆጥራቸው።


ፊደል ፖስት: በአሁኑ ሰአት እንደማንኛውም የሀገሪቱ ሰራተኛ የአየር መንገድም ሰራተኛ ኮሮና የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ከጎዳ ስራ ላልመልስ እችላለው ብሎ ሰግቷል ።በዚህ ላይ ያላቹ አስተያየት ምንድን ነው?

ማርቆስ የሱወርቅ: እንግዲህ ይሕ በግልፅ መመለስ የሚችለው የድርጅቱን ኢኮኖሚያዊ አቅም በሚያውቅ አካል እና በሚደረጉ ጥናቶች ነው።

አስተያየት ለመስጠት ያክል ግን፤
አንደኛ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም ዓቀፍ የማጓጓዝ ንግድ ላይ የተሰማራ የልማት ድርጅት እንደመሆኑ መጠን ይሕ ወረርሽኝ አልፎ ዓለም ዓቀፍ ዝውውሮች ወደነበሩበት ሲመለሱ ወደ ተለመደ ወይም ወደተሻለ የንግዱ ዑደቱ ይመለሳል ብለን እናምናለን።

ሁለተኛ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አንድ የንግድ ማእከል ብቻ ያለው ድርጅት አይደለም። መንገደኞችን ከማጓጓዝ ባሻገር እንደ ካርጎ ማጓጓዝ እና ጥገና ክፍል የመሳሰሉ የንግድ ማእከላት ያሉት ድርጅት ነው። እነዚህን ማእከላት በመጠቀም ቀጣይነትን ማረጋገጥ ይቻላል ብለን እናስባለን።

አየር መንገዱ ባሳለፋቸው አያሌ ዓመታት የተለያዩ ችግሮች ገጥመውት ያውቃሉ ፤ በመተባበርም አልፈዋል። በእርግጥ ይኼኛው ችግር እስካሁን ከመጡት ሰፋ ያለ ቢሆንም ከየትኛውም ቦታ የተሻለ የስራ ባህል ያላቸው ታታሪ ሰራተኞች ስላሉት ይህንን ግዜ እናልፈዋለን ብለን እናምናለን።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንግድ በዓለም የንግድ እና የ ጉዞ እንቅስቃሴ ላይ የተመረኮዘም ስለሆነ የዓለም የንግድ እና የጉዞ እንቅስቃሴ በጥቂት ግዜያት ወደነበረበት የሚመለስ ከሆነ ለሰራተኛው ስጋት አይሆንም ብለን እናምናለን።

ከዚህ ውጪ የወረርሽኙ ስፋት ጨምሮ እና ግዜውም ረዝሞ ዓለም ዓቀፋዊ ድቀት የሚያመጣ ከሆነ ከዓለም ተለይተን የምንኖር ስላልሆንን ሊከብደን ይችላል።

ያ እንዳይሆን ግን እኔም ወደፈጣሪ ፀሎቴ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *