በማይካድራ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር ሊያሻቅብ እንደሚችል ተገለፀበማይካድራ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር ሊያሻቅብ እንደሚችል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አፈፃፀም እየመረመረ ያለው ቦርድ ገልጿል፡፡

መርማሪ ቦርዱ ሰሞኑን በማይካድራ ከተማ ባደረገው የመስክ ምልከታ በከተማዋ ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም ስለተፈጸመው አሰቃቂ የግድያ ወንጀል በቦታው ተገኝቶ መረጃ ሰብስቧል።የመርማሪ ቦርዱ አባላት ከ50 እስከ 60 አስከሬኖች በአንድ ላይ የተቀበሩባቸውን ቦታዎች ተዘዋውረው መመልከታቸውን ገልፀዋል፡፡

መርማሪ ቦርዱ ባገኘው መረጃ የሟቾቹ ቁጥር ቀደም ሲል የተለያዩ ሚዲያዎችና የሰብዓዊ መብት ተቋማት ከጠቀሱት ሊያሻቅብ እንደሚችል ተገልጿል፡፡የምርመራ ቡድኑ አባላት በአካባቢው ከሚኖሩ ሰዎች ጥቆማ ደርሷቸው በአካባቢው የሚገኘው ጊዜያዊ አስተዳደር ገና ያልደረሰባቸውና አፈር ያልለበሱ አስከሬኖችን መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡ጥቃቱ በአካባቢው የነበረው የሚሊሻና የፖሊስ ጸጥታ መዋቅር አከባቢውን ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ለቆ ሸሽቶ ከመውጣቱ በፊት “ሳምሪ” ከተባለ መደበኛ ያልሆነ የትግራይ ወጣቶች ቡድን ጋር በማበር የፈጸሙት ወንጀል ስለመሆኑ ቦርዱ ማረጋገጥ ችያለው ብሏል፡፡

በአንጻሩ አጥቂው ቡድን ሲያሳድዳቸው የነበሩ ሰዎችን በቤታቸው፣ በቤተክርስቲያንና በእርሻ ቦታዎች በመደበቅ የብዙ ሰዎች ህይወት እንዲተርፍ ያደረጉ የትግራይ ተወላጆችም መኖራቸውን መርማሪ ቦርዱ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡የመርማሪ ቦርዱ አባላት ተጎጂዎቹ በብዛት በሚኖሩበትና በተለምዶ “ግንብ ሰፈር” በተባለው አካባቢ ተገኝተው ከሟች ቤተሰቦችና ከግድያ ሙከራው ከተረፉ ሰዎች ጋር ውይይት አድርገዋል።የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ለማ ተሰማ ከጉዳቱ ሰለባዎች ጋር በተወያዩበት ወቅት፤ መንግስት ወንጀለኞቹን አድኖ ለፍርድ እንዲያበቃ ለማገዝ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *