የሆነው ነገር አንዲህ ነው ። በሸገር ፖርክ ሜዳ ላይ በኤል ቅርፅ ከተሰራቸው ነጭ ድንኳን ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ባለቤታቸው ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸውን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ባለልጣኖች ከፊታቸው በግምት 130ሜትር እርቀት ላይ በተሰራው እስቴጅ ላይ በመድረክ መሪዎቹ አበበ ፈለቀ እና ጥላሁኑ ጉግሳ የሚተዋወቀውን የበአል ዋዜማ ምሽት ፕሮግራም እየሰሙ ዝግጅቱን እየታደሙ ነበር።
ምሽት ሶስት ሰዓት ካለፈ በኋላ ጠ/ ሚ ዐቢይ አህመድ ወደ መድረክ በቴሌዘቭዥን በቀጥታ በሚተላለፈው ፕሮግራም ለህዝባቸው ንግግር ለማሰማት መጡ ። ንግግር የሚያደርጉባት ፖዲየም ከእንግዶቹም 10 ሜትር እርቀት ላይ ነበረች ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በእጃቸው ማይኩን መታ ሲያደርጉት ጠንከር ያለ ድምፅ ባለመውጣቱ ከጅምሩ ምቾት አልተሰማቸውም ነበር። ንግግራቸውን እንደጀመሩ ገመድ አልባው ማይክራፎን ተቆራረጠ። ችግሩ ደግሞ የማይክራፎኑ ሲግናል መቀበያ ከመድረክ ስለነበረ ጠ/ ሚኒስትሩ ደግሞ እርቀው ስለነበረ ማይኩ ሊሰራ አልቻለም ። ሳውንድ ሲሰተሙን የዘረጉት ሰዎች ቀድመው ሙከራ ቢያደርጉ ኖሮ ችግር አይገጥምም ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የማይኩን አፍ እየመቱ ቢሞክሩ እንቢ አለ ። ወደ መቀመጫቸው በጠባቂዮቻቸው ታጅበው ተመለሱ። በፋና ፣በዋልታ ፣በኢቲቪ በቀጥታ ይሰራጭ የነበረው የቴሌቭዥን ፕሮግራም ተቋረጠ። በቴሌቭ ዥን ፕሮግራሙን ለሚከታተል ሰው የጠ/ ሚኒስትር ፕሮግራም ሲቋረጥ ሌላ ነገር የተፈጠረ ነበር የሚመስለው ።
የድምፅ ሲስተሙን ለማሰተካከል ተሞከረ ።እንቢ አለ።
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢ/ር ሀብታሙ ተገኝ ፣የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ የብልፅግና ፓርቲ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ስቪክ ማኅበራት ጉዳዮች ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር ዓለሙ ስሜ እንዲሁም የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትሯ ወ/ሮ ደሚቱ ሀምቢሳ የማይክራፎኑን ችግር ለመፍታት በእንግድነት ከተቀመጡበት ድንኳን ወጥተው ውር ውር ማለት ጀመሩ ። ወደ መድረክ በመምጣት ችግሩን ለመፍታት ከመድረክ አስተናባሪዎች ጋር ማውራት ጀመሩ ።
መድረክ ላይ የነበረችውን ሲግናል መቀበያ ወደ ፖድየሙ ለማቅረብ ተሞከረ ።ነገር ግን ፖድየሙ እርቆ ስለነበረ ማይኩ በቂ ድምፅ ሊያወጣ አልቻለም።
በመጨረሻም ከአንድ ሀሳብ ተደረሰ ።ለሙዚቃ ወደተሰናዳው መድረክ ላይ ጠ/ ሚሩን ማምጣት ። ይሄን ለማድረግ መድረኩ ላይ የነበሩትን የሙዚቃ ተጫዋቾች እና ከመድረክ ጀርባ የነበሩት ወደ መቶ ገደማ የሚጠጉ ተወዛዋዦችን መድረኩን አንዲለቁ ተደርጉ ።
ዶክተር ዐቢይም ” እንዲህ ያለ የአማረ መድረክ እያለ ተናገር በማለት ነው ” ብለው በማሳቅ የተፈጠረውን ችግር ረስተው ዳግም ከ15 ደቂቃ በኋላ ንግግር ጀመሩ ።
ሲጨርሱም አንግዶች ከመድረኩ እረቀው ስለነበር ዘገም ባለ ሩጫ በጠባቂዎቻቸው ታጅበው ወደ ድንኳን ሲያመሩ ሰውን አስቀው ነበር ። በእርግጥ ይሄን ያደረጉት ሰው ቆሞ እያጨበጨበ ወደ መቀመጫቸው እየሸኛቸው ስለነበር ሰውን ብዙ ላለማስቆም ነው ።
በትላልቅ ፕሮግራሞች ላይ መብራት መጥፋት ፣ማይክ አለመስራት በተደጋጋሚ እያጋጠመ ያለ ችግር ስለሆነ አስቀድሞ መዘጋጀት ፣አስቀድሞ መሞከር የትናንትናው የዋዜማው ምሽት የሸገር ፓርክ ዝግጅት ትምህርት ሰጥቶ አልፏል።