” የላዳ ታክሲዎችን እንጀራ አልቀማውም።የተሻለ ቴክኖሎጂ ለሀገሬ አስተዋወቅኩ እንጂ ” የራይድ ትራንስፓርት ቴክኖሎጂ ባለቤት ሳምራዊት ፍቅሩ


ከአምስት አመት በፊት ብቻዋን ሆና አንድ ወንበር ፣አንድ ሼልፍ እና በሁለት ጠረጼዛ የSMS ሎተሪ ,የጥገና ማኔጅመንት ሲስተም, ድህረ ገፆች የምትሰራ ሴት ነበረች ። ነገር ግን የሜትር ታክሲን ራይድ በተባለ አፕሌክሽን አዘጋጅታ ለገበያ ማቅረቧ የ11,000 መኪኖችን ልብ ማርካ የሜትር ኪራይ መኪናን አገልግሎትን ቴክኖሎጂን በማስተባበበር ለሺ ዎች ስራ ፈጥራለች። በአዲስ አበባ ” ራይድ ” ልክ እንደ” ኮካ ኮላ” የሚታወቅ ስም ሆኗል ። ዛሬ ቢሮዋ ሰፍቶ በሚያምር ምንጣፍ እንግዶቿን የምትቀበል ሴት ሆናለች ።ቢሮዋ ብታቀኑ የሚያነጋግራት እንግዳ ከመብዛቱ የተነሳ ቢያንስ ይህቺን ሴት ለማናገር አንድ ሰአት ተኩል መጠበቅ ይኖርቦታል ።የፊደል ፓስት ዋና አዘጋጅ ተስፋዬ ጌትነት ቢሮዋ አቅንት ሳምራዊት ፍቅሩን በራይድ ትራንስፓርት ቴክኖሎጂ ላይ አነጋግራቷል ።ቃለ ምልልሱ በአጭሩ ይሄን ይመስላል ።

ፊደል ፓስት: ይሄን ስራ ከመጀመርሽ በፊት አሜሪካ ውስጥ” የኡበር” ታክሲ ሹፌር ነበርሽ ተብሎ ይወራል እውነት ነው እንዴ?
ሳምራዊት: ( ሳቅ) እረ በጭራሽ ። የሆነ ግዜ ካሜሮን አገር ሄጄ ለሰባት ወር የጌም ሲስተም ልሰራ ሄጄ ነበር ።አሜሪካም ሄጄ አላውቅም ። የራይድ ሀሳብ የመጣልኝ የመጀመርያ ስራዬን ስሰራ አምሽቼ በላዳ ታክሲ ነበር የምሄደው ።ግን ስጋት ነበረብኝ ።ወንጀል ቢፈፀምብኝስ ብዬ አስብ ነበር ። ይሄም ስጋት የብዙ ሰው ሆኖ ተመለከትኩኝ ።አንድ ሀሳብ መጣልኝ ።ለምን አድራሻው የሚታወቅ ፣በተመጣጣኝ ዋጋ የሚወስድ ትራንስፓርት ሲስተም አልዘረጋም አልኩኝ ።አሁን በኢንተርኔት እና በስልክ ተደውሎ ያለህበት ድረስ የሚመጣውን የራይድ አገልግሎትን በSMS አስጀመርኩኝ ።ከዛም ሞባይል ላይ በሚጫን አፕ አሳድጌ ይኸው ዛሬ የምታየውን ሆኗል።

ፊደል ፓስት: የራይድ ትራንስፓርት ከመጣ በኋላ የላዳ ታክሲ ሹፌሮች እንጀራችን ቀማችን ብለው ያማራሉ ለዚህ ያለሽ ምላሽ ምንድን ነው?
ሳምራዊት: እኔ አልቀማውም! ሰው የሚያገኘውን የትራንስፓርት አገልግሎት ቀላል እና ፈጣን ነው ያደረኩት ።ሰው ቤቱ ቁጭ ብሎ የሚፈልግበት ቦታ እንዲደርስ ማድረግ ሊመሰገን የሚገባው ተግባር ነው ።ራይድ 11,000 ሰዎች ስራ ፈጥሮ ስታይ ፣ እህቶቻችን አረብ ሀገር ሰርተው ይገኙትን ትንሽ ብር ምን ላርግ ብለው ተጨንቀው እዚህ መኪና ገዝተው በራይድ ገቢ ሲያገኙ ስታይ ተጨማሪ እንጀራ አስገኘን እንጂ እንጀራ አንዳልቀማን ትረዳለክ ።መቼም አዲስ ነገር ሲመጣ ለመቀበል አዳጋች የሚሆንበት ግዜ አለ ።ግን በአንድ አይነት ሲስተም ሁሌ መኖር የለብንም ራሳችንን ማደስ መለወጥ ያስፈልጋል ።የአደጉት ሀገራት ተሞክሮም ይሄ ነው። የላዳ ታክሲዎች ወደ እኛ ሲስተም እንዲገቡ እየጣርን ነው ።ከባንክ ብድር አግኝተው ሌላ መኪና ገዝተው የራይድ አገልግሎት እንዲሰጡ አየጣርን ነው።
ፊደል ፓስት: የራይድ ሹፌሮች አንዳንዴ በላዳ ሹፌሮች ጫና ሲደረግባቸው ይታያል ።ይሄን እንዴት ታይዋለሽ ?
ሳምራዊት: ይሄ አግባብ አይደለም ።ሰዎች በሀገራቸው የመስራት መብት አላቸው ።” ዱካ ” የተባለ አዲስ የደህንነት መጠበቂያ ሲስተም እየዘረጋን ነው ።የራይድ ሹፌሮች ምንም አይነት አደጋና ስርቆት ቢደርስባቸው “ዱካ ” ድረሱልኝ ብላ አካባቢው ላሉ ፓሊሶች ፣የራይድ ሹፌሮች ፣ሰዎች ታሳውቃለች ።ይሄም የራይድ ቤተሰቦችን ደህንነትን በይበልጥ ይጠብቃል።
ፊደል ፓስት: ” ዱካ ” ዋጋዋ 6,500 ብር ነው ካልተሳሳትኩ ።የራይዳ ቤተሰቦች ዋጋው ተወደደ ሊቀንስ ይገባዋል ሲሉ ይደመጣሉ ።በዚህ ላይ ያለሽ ምላሽ ምንድን ነው?
ሳምራዊት: ይሄን ብር በአንዴ ክፈሉ ብለን አላስገደድንም። በወር 1,200 ብር እየከፈሉ በስድስት ወር እንዲከፍሉ ለፋይዳ ከተባለ ማይክሮ ፋይናንስ ጋር ተሳምምተናል። ስለዚህ በዚህ በመጠቀም ክፍያቸውን ማቅለል ይችላሉ ።
ፊደል ፓስት: የራይድ ሹፌሮች አሁን ያለው በኪሎ ሜትር 10 ብር ዋጋ ትንሽ ከፍ ብሎ ከ 13 እሰከ 15 ቢሆን ወቅቱን ያገናዘበ ነው ይላሉ ።ምላሽሽ ምንድ ነው ?
ሳምራዊት: እውነት ለመናገር ሂሳቡን ከፍ የማረግ እቅድ አሁን የለንም ። ወደፊት ግን የምናሰብበት ይሆናል ።
ፊደል ፓስት: በአንድ ወቅት የራይድ መኪኖች አንድ አይነት ቀለም ሊቀቡ ይገባል የሚል የመንግስት አቋም ነበር ። ምን ላይ ደረሰ ይሄ ጉዳይ ?

ሳምራዊት: ራይድ የኪራይ አገልግሎት ነው ።ስለዚህ የኪራይ መኪኖች ቀለም ይቀቡ የሚል ህግ የለም ።ስለዚህ ቀለም አይቀቡም ማለት ነው ።

ፊደል ፓስት: አዲስ ኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ ፓርላማው አፅድቋል ።ይሄም ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡትን አሮጌ መኪኖች ላይ ከፍተኛ ታክስ ስለጫነ የመኪኖችን ወደ ሀገር ውስጥ መግባት ይቀንሳል ።ከአንቺ ጋር የሚሰሩ የራይድ መኪኖች አብዛኞቹ አዲስ መኪኖች አይደሉም ።ይሄ አዋጅ ለወደፊት ስራሽ ላይ ተፅእኖ አይኖረውም ?
ሳምራዊት: አሮጌ መኪና ወደ ሀገር ውስጥ አለመግባቱ የአካባቢ ብክለትን ይቀንሳል ።ለመለዋወጫ እቃ ለማስመጣት የምናወጣውን ዶላርንም ይቀንሳል ።አኛ እንደውም አሁን ያሉትን የራይድ መኪኖች ወደ ኢኮኖሚ ደረጃ ሄደው ከባንክ ብድር አመቻችተን በአዲስ መኪና የመተካት እቅድ አለን ።
ፊደል ፓስት: አሁን 11,000 መኪኖች ካንቺ ኩባንያ ጋር አበረው ይሰራሉ ሌላ ሺዎች መኪኖች ቢመጡብሽ አቅሙ አለሽ ለማስተናገድ ።
ሳምራዊት: በደንብ ነዋ! አዲስ አበባ 2.4 ሚልየን ህዝብ በትራንስፓርት ይቸገራል ስለዚህ ይሄን ህብረተሰብ ፍላጎቱን ለሟሟላት ገና ብዙ ስራ ይቀረናል። ከአንዳንድ የክልል ለተሞችም ጋር አብሮ ለመስራት ስምምነት አርጊያለው ሰአቱ ሲደርስ ምናገረው ይሆናል።
ፊደል ፓስት: ሌላ በተሻለ ለማዘመን ምን እየሰራሽ ነው ?
ሳምራዊት: አገልግሎቱን ከማስፋት በተጨማሪ የራይድ ተጠቃሚዎች በአሁኑ ሰአት ለተጠቀሙት አገልግሎት ጥሬ ብር ነው የሚከፍሉት ይሄ መቅረት አለበት ብለን አስበናል ።” ብሬ ” የተባለ የአካፋፈል ስርአት ለመዘርጋት እየሰራን ነው ።ይሄም ተጠቃሚዎች ለራይድ ሹፌሮች ብር ሳይከፍሉ ከባንክ ሂሳባቸው ላይ የተጠቀሙበትን የትራንስፓርት ክፍያ የሚወስድ ነው።
ፊደል ፓስት: የአንቺን ኩባንያ አገልግሎት አይነት የሚሰጡ አዳዲስ ካምፓኒዎች እየመጡ ነው ።እንዴት ታይዋለሽ?
ሳምራዊት : በርቱ ነው ማለት ምፈልገው ።ገና መች ተሰራና!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *