እንደዚህም አልቅሰን እንደዚህም በግፍ ተገለን አናውቅም ።የካቲት 12 ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ!



የ83 አመት ታሪክ ነገር ግን በሰማነው ቁጥር እንደ ትኩስ ለቅሶ ነው ሚሆንብን። ።ከ30,000 በላይ የሀገራችን ዜጎች በፋሽስት ጣልያን ሰው መግደል ከዶሮ ማረድ ቀሎ በአንድ ቀን ተገደሉ ተብሎ መስማት መራር ሀዘን ተብሎ በቃል የሚገለፅ አይደለም ። ሊያውም ሊገዙን በመጡ ወረሪ ሀይሎች በገዛ ሀገራችን ሬሳ እያስቆጠሩን ህፃን፣አሮጊት፣ሽማግሌ፣ጎልማሳው በሽተኛው ሳይቀር በግራዝያኒ ወታደሮሽ ተረሽዋል ። የአካለ ጉዛይና የከማሲው ( አሁን በኤርትራ ግዛት የሚገኙ) ሞገስ አስገዶም እና አብርሃ ደቦጭ በጣልያን ዳግም መወረራችን ሳይዋጥላቸው ግራዝያኒ ላይ ዛሬ ስድስት ኪሎ ዩንቨርስቲ ተብሎ በሚጠራው ቦታ ቦንብ ወርውረው አቆሰሉት ።አፀፋው ግን የከፍ ነበር ።ናዚ አይሁዶች ላይ የሰራውን አፀያፊ ተግባር ።የግራዝያኒ ወታደሮችበኢትዮጵያ ላይ ደገሙት ።ሰው በሬሳ አየተረማመደ መልሶም እርሱ ወደ ሬሳ እየተቀየረ ።ጨለማ ቀን የካቲት 12,1929 በኢትዮጰያ ጨለማ ቀን ሆኖ ዋለ ።በእውነትስ እንደዚህ ተገለን አናውቅም ።እንደዚህም አልቅሰን አናውቅም ።
ጋዜጠኛው ጳውሎስ የኢትዮጵያ እና የኢጣልያ ጦርነት 
በሚለው መፅሀፉ ቀኑን እንዲህ ያስታውሰናል ;
“የኔፕልስ ልዕልት በመወለዷ ግራዚያኒ የደስታ መግለጫ ገንዘብ እሰጣለሁ ብሎ ከዛሬው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከድሮው ቤተመንግስት ድሆች እንዲሰበሰቡ አዘዘ። ከድሆቹ በስተቀር ታላላቅ የኢጣልያ ሹማምንት፣ የሜትሮፖሊታን ጳጳስ አቡነ ኪርልና ሌሎችም መኩአንንት ነበሩ። ለእያንዳንዱ ድሀም ሁለት ማርትሬዛ ብር እንዲሰጥ ተወስኖ ነበር።


እኩለ ቀን ገደማ ላይ 3000 የሚሆኑ ድሆች ከቤተ መንግስቱ ገቡ። ወዲያው በግቢው በር በኩል አንድ ቦምብ ፈነዳ። ቀጥሎም ሌላ ፈነዳ። ለሶስተኛ ጊዜ የተጣለው ቦምብ የፋሺስት ኢጣልያ መክዋንንት ካሉበት ቦታ ፈነዳ። ግራዚያኒ ጀርባውን ቆስሎ ወደቀ። በቀጠለው ጥቂት ደቂቃ ውስጥ ሌሎች ቦምቦች ተከታትለው ተጣሉ። በጠቅላላው በግቢው ውስጥ ሰባት ቦምቦች ፈነዱ። ጄኔራል ሊታዩ፣ የአዲስ አበባው ከንቲባ ጉይዶ ኮርቴሲ፣ ጋዜጠኛው ማርዮ አፔሎስ እና ሌሎች 30 ያህል ሰዎች ቆሰሉ። የቦምቡ ፍንዳታ ጋብ እንዳለ አድፍጠው ተኝተው የነበሩ ወታደሮች ተነስተው ተኩስ ከፈቱ። በዚያ ግቢ ውስጥ ያለማቁዓረጥ ሶስት ሰዓት ሙሉ ተኩስ ተካሄደ።


ከጥቂት ጊዜ በህዋላ ባለ ጥቁር ሸሚዞች፣ የኢጣሊያ ሾፌሮች፣ የቅኝ ግዛት ወታደሮች በአዲስ አበባ ከተማ እየዞሩ ሕዝቡን ይፈጁት ጀመር።

የካቲት 12 ቀን በተጀመረው እልቂት በሶስት ቀን ውስጥ 30000 ሰዎች በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ከተገደሉ በህዋላ ሌላው እየታፈሰ ወደ በረሃ እስር ቤቶች ተላከ። እስር ቤቶቹ እንዴት ነበሩ? ለጦር ወንጀለኞች አጣሪ ኮሚቴ፣ ብላታ በቀለ ሃብተ ሚካኤል ከተናገሩት ውስጥ በመጠኑ እንጥቀስ። “… መቃዲሾ እንደደረስን በቀጥታ ከዋናው ወህኒ ቤት አገቡን። በማግስቱም ወደ ደናኔ ወሰዱን። 200 ሰዎች ባንድ ቦታ አጎሩን። ይሰጡን የነበረው ምግብ ለጤናችን ፈፅሞ የማይስማማ ነበር።”


“የሚሰጡንም በላዩ ላይ ብዙ ትላትሎች የሚታዩበት የደረቀ ቂጣና ሻይ ነበር። በዚህም ምክንያት ብዙዎቻችን ታመምን። የዚያን ጊዜ የእስር ቤቱ ኃላፊ ብርጋዴር ባሮኒ ነበር። ስለምግባችን ብዙ ጊዜ እየቀረብን ብናመለክትም ትዕዛዙ የበላይ ስለሆነ ምንም ማድረግ እንደማይቻል ይነግረን ነበር። በግራዚያኒ ሕይወት ላይ አደጋ ከተጣለ በህዋላ ብዙ እስረኞች ወደኛ መጡ። ቦታ ስለጠበበ ሜዳው በሽቦ ታጥሮ ከዚያ ሰፈሩ። እኛንም ወስደው ከነሱ ጋር ደባለቁን። ከተደባለቅን በህዋላ የምግብ ጉዳይ የባሰ ሆነ። በምግቡ ምክንያት በየቀኑ አራትና አምስት ሰዎች እየሞቱ ይጣሉ ጀመር…” ብለዋል። የተባበሩት መንግሥታት ከተመሰረተ በህዋላ በዚሁ ስር ለተቁዋቁዋመው አጣሪ ኮሚሽን ቃላቸውን ከሰጡት እስረኞች መሃል ሌላው አቶ ሚካኤል ተሰማ ናቸው። እሳቸው እንዲህ ብለው ነበር “… በደናኔ እስር ቤት ሶስት ዓመት ከሶስት ወር ታስሬ ቆይቻለሁ። የወህኒ ቤቱም ሁኔታ እንዲህ ነበር። ላንድ ወታደር ማደሪያ የተሰራች አንዲት ድንክዋን ለሶስት ኢትዮጵያውያን ተሰጠችን። ምግባችን የደረቀ ጋሌታ ነው። የውቅያኖሱን ውሃ መጠጣት እንደጀመርንም ብዙዎቻችን ታመምን። በየቀኑ ከስድስት እስከ ሰላሳ ሰዎች በተቅማጥ በሽታ ይሞቱ ነበር። በጠቅላላውም 3175 ሰዎች ሞቱ። ይህንንም ቁጥር ለማወቅ የቻልኩት በክሊኒኩ ውስጥ ረዳት ሀኪምና የበሽተኞች ሁኔታ መዝጋቢ ስለነበርኩ ነው። በደናኔ እስር ቤት የነበርነው 6500 ሰዎች ነን። ከነዚሁ ውስጥ 3175 ሰዎች ሞቱ። ዓመት ከታሰርን በህዋላ ስጋ፣ ማካሮኒ እና ሩዝ በሳምንት አንድ ጊዜ ይሰጠን ጀመር። እስረኞቹን ይጠብቁ ከነበሩት ኢጣልያኖች መሃል ብርጋዴር ባሮኒ፣ 50 አለቃ ቶሳቶ እና አሁን ስሙን የረሳሁት የካራሚኔሪዎች ማርሻል እስረኞቹን በመግረፍ የታወቁ ነበሩ።”

ግራዚያኒ የየካቲት 12 ቀንን እልቂት ባዘዘ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ የነበረው የኢጣልያ ወታደር 35000 ሜትሮፖሊታን ወታደሮች፣ 40000 ባለጥቁር ሸሚዝ ሚሊሺያ፣ 5000 የኤርትራ፣ 3000 የሊቢያ ተወላጅ ወታደሮች ነበሩ። የኤርትራ ተወላጅ ወታደሮች “እኛ ወታደሮች ነን። ከተማ ውስጥ ከሴትና መሳሪያ ከሌለው ጋር በጥይት ተኩስ አንተኩስም” በማለታቸው ብዙዎቹ ጦር ሰፈራቸው ውስጥ ተገደሉ። ሌሎችም ታሰሩ።


የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. ዛሬ ዩኒቨርሲቲ በሆነው ግቢ ውስጥ ቦምቦች ሲፈነዱ ቦምቦቹ የተጣሉት ከሁለት ይሁን ከብዙ ሰዎች እስካሁን የታወቀ መረጃ የለም። ግራዚያኒ አጠገብ የፈነዳውን ግን አብርሃ ደቦጭ ከጉዋደኛው ከሞገስ አስገዶም ጋር እንደጣለው ይነገራል።”
ይሄም ግፍ የተሰራባት ኢትዮጵያ አልጠፋችም ።ቀኑን ግን ዝንት አለም ስትዘክረው ትኖራለች ።የካቲት 12 ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ!!!





Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *