አዲስ ዘመን ጋዜጣ፤ በጥር 6, 2012 ዓ.ም ዜናው የሚከተለውን ለህዝብ አስነብቧል።

“የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም፤ ከሰሞኑ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለቀረበላቸው አስተያየትና ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ፤ አየር መንገዱ ለስኬታማነቱ ትልቁ ሚስጥሩ ሥነምግባር እንደሆነ ገልፀዋል:: ነገር ግን በአገሪቱ ካለው የሥራ ባህል አንፃር ይህ የማይዋጥላቸውና ምቾት የሚነሳቸው ሠራተኞች አይጠፉም::

አራት መቶ መንገደኞችን ይዞ ከባህር ወለል 40 ሺህ ጫማ ከፍታ ላይ የሚበር አውሮፕላን የሚጠግን ቴክኒሺያን ትንሿ ስህተት ሕይወት ልታስከፍል ስለምትችል ከፍተኛ ጥንቃቄ ይጠበቅበታል:: በዚህ ደረጃ ሕጉን ለማስፈፀም ጠንከር ያሉ እርምጃዎች ሲወሰዱ ደግሞ ቅሬታዎች ይበዛሉ::”

በዚህም መሰረት ይሕንን ግልፅ የሆነ መግለጫ ማውጣት አስፈላጊ ሆኖ አግኝተነዋል።

እኛ የኢትዮጲያ አቪየሽን ቴክኒሽያኖች በየትኛውም አለም የአቪየሽንን የደህንነት መርሆች በመጠበቅ እና በማስጠበቅ ውስብስብ የሆኑ ችግሮችን በአጭር ግዜ ውስጥ ለመፍታት ብቁ የሆንን እንዲሁም ለአለም አቀፍ የአቪየሽን ደህንነት መርሆች ትኩረት በመስጠት የአለም አቀፉን ተጓዥ ደህንነት በሚገባ እያስጠበቅን ያለን ባለሙያዎች ስንሆን ፤ በዋናነትም ኢትዮጲያ በአቪየሽን ዘርፍ አሁን ላለችበት ደረጃ የጀርባ አጥንት ሆነን የዘለቅን እና ለሀገራችን አቪየሽን ዘርፍ ሰፊ ራእይ ሰንቀን ይሕንን የምንቀጥል ዜጎች ነን።

ነገር ግን በዚህ አዲስ ዘመን ባስነበበው እትም የተገለፁት ነገሮች ፤ በምንም አይነት ሙያውንም ሆነ ባለሙያውን የማይወክሉ ናቸው ብለን እናምናለን። ይሕም በዚህ ዜና ላይ የተገለፀው የዋና ስራ አስፈፃሚው ንግግር ፤ በድርጅቱ ውስጥ በአውሮኘላን ጥገና ላይ የተሰማራውን ሀገሩን የሚወድ ትጉህ ባለሙያን የሚንቅ እና የሚያዋርድ እንደሆነ በግልፅ ተረድተናል። እኛ ሁላችን ሙሉ በሙሉ የአየር መንገዱ ሰራተኞች ስንሆን ፤ ቅሬታዎች እንደሚኖሩ የማይካድ ነው። ነገር ግን ይሕ የተጠቀሰው ንግግር ፤ “የቴክኒሽያኑ ቅሬታ የሚመነጨው የደህንነት መርሆችን ባለመከተሉ ምክንያት በሚወሰደው እርምጃ ብቻ ነው።” የሚል አንድምታ የሚፈጥር እና “ቴክኒሽያኑ የአቪየሽን ደህንነትን ለማስጠበቅ ሲባል የሚወጡ ህጎችን (Safety procedures) የመከተል መሰረታዊ ችግር አለበት እንዲሁም ለዚህ ብቁ ባለመሆኑ ምክንያት ብዙ እርምጃዎች ይወሰዱበታል።” የሚል ትርጉም አለው ብለን እናምናለን።

ይሕ በሙያተኛው እና በሙያው ላይ የተደረገ ከፍተኛ የንቀት ፣ የስም ማጥፋት እና አግባብ ያልሆነ ውንጀላ ነው ብለን ስለምናምን ተቀባይነት የለውም።

ያለመታከት ለሀገሩ ብልፅግና ፣ ለአየር መንገዱ ልእልና ብሎም ለአለም አቀፉ ተጓዥ ደህንነት የሚለፋውን ባለሙያ በዚህ መልኩ መወንጀል መሞከር እጅግ የሚያሳዝን እና በተለይም በዋና ስራ አስፈፃሚው ሲደረግ እጅግ ሞራል የሚነካ ነው።

ቴክኒሽያኑ በሙሉ ማንኛውንም ዕፀፆች የውስጥ ገመና ነው በሚል እሳቤ ወደ ውስጥ በመያዝ የተሻሉ ነገሮችን ለማምጣት እየተጋ ባለበት በዚህ ሰአት በዚህ መልኩ የቴክኒሽያኑ እና የሙያው ክብር በህዝብ ፊት መዋረዱ አሳዝኖናል። የቴክኒሽያኑ በህዝብ ፊት በዚህ መልኩ መቅረብ ለአየር መንገዳችንም ቢሆን ስሙን የሚያጎድፍ ነው ብለን እናምናለን።

ሙያው እጅግ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚፈልግ መሆኑን የምንረዳ ፤ ይሕንን ለማድረግ የሙያው ስነ-ምግባር እና ያለን በቂ እውቀት የሚያስገድደን መሆኑ ፤ እንዲሁም ነገሮች ባለተሟሉበት ሁኔታ እያንዳንዱ ቴክኒሽያን ከፍተኛ በሆነ የግል ጥረትም ጭምር የበረራ ደህንነትን አስጠብቆ፤ ለሀገሪቱ እና ለአየር መንገዳችን ዋልታ የሆነ ባለሙያ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል።

የበረራም ደህንነት በበቂ ሁኔታ የሚጠበቀው ጠንካራ እርምጃ በሚወስዱ አሰሪዎች ብቻ ሳይሆን ፤ በሙያ በበለፀጉ፣ በእውቀት እና በመልካም ስነምግባር በታነፁ ቴክኒሽያኖች ነው ብለን እናምናለን።

በዚህም አጋጣሚ፤ እኛ የአውሮኘላን ጥገና ባለሙያዎች በዚህ ነገር ሞራላችን ሳይነካ ለሀገራችን አቪየሽን ዘርፍ እንዲሁም ለውዱ አየር መንገዳችን የሰነቅነውን ራእይ ከግብ ለማድረስ በትጋት መስራት እና ለደህንነት ምክንያት መሆናችንን አጠናክረን መቀጠላችን የአማራጭ ጉዳይ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ መሆኑ ለማረጋገጥ እንወዳለን!!!!

ክብር_ለባለሙያው!

RESPECT_TO_THE_PROFESSIONAL!

የኢትዮጲያ አሺየሽን ቴክኒሽያኖች ማህበር
ጥር , 2012 ዓ.ም

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *