አውታር መልቲ ሚዲያና ቢ ጂ አይ ኢትዮጵያ የ5 አመት ስምምነት ተፈራረሙ።

አውታር መልቲ ሚዲያና ቢጂ አይ ኢትዮጵያ ያደረጉት የአምስት አመት ስምምነት ለሙዚቃው ገበያ በባለሙያዎች ተሰርተው በአውታር መተግብሪያ በኩል ለገበያ የሚቀርቡ ማንኛውም የሙዚቃ ስራዎች ለሕዝብ በቀላሉ ለማስተዋወቅ እንዲቻል በቢል ቦርድ፣በፖስተርና በተለያዩ ህትመቶችና የማስተዋወቂያ መንገዶች ላይ ፍትሀዊ በሆነ፣በተቀናጀ እና ቋሚ በሆነ መልኩ ሁሉም ድጋፍ እንዲያገኙ የሚረዳ አሰራርን የሚያስተዋውቅና ሙዚቀኞች አትኩሮታቸውን ሙዚቃ የማምረት እና መብታቸውን በማስከበር ስራ ላይ በማድረግ የሙዚቃ ስራቸውን ለህዝብ የሚያስተዋውቁበትን አማራጭ የሚሰጣቸው ይሆናል ተብሏል።

አውታር መልቲ ሚዲያና ቢጂ አይ ኢትዮጵያ ያደረጉት የአምስት አመት ስምምነትን ትናንት ምሽት በሸራተን አዲስ ላሊበላ አዳራሽ ሲሆን ሁለቱ ተቋማት የስምምነት ፊርማውን በተፈራረሙበት ወቅት እንደተነገረው ስምምነቱ ብዙ ተግዳሮቶችን ለማቅለል መንገድ እንደሚከፍት የአውታር መልቲ ሚዲያ መስራችና ስራ አስኪያጅ ድምጻዊ ዮሀንስ በቀለ (ጆኒ ራጋ) እና የቢጂአይ ኢትዮጵያ ኮሜርሻል ህዝብ ግንኙነት ሀላፊ የሆኑት አቶ ገብረስላሴ ስፍር ተናግረዋል። ስምምነቱን ድምጻዊ ሀይሌ ሩትስን ጨምሮ ሁለቱ የስራ ሀላፊዎች በፊርማቸው አጽድቀዋል።

በፈርማ ስነስርአቱ ላይ የአውታር መልቲ ሚዲያና እና የቢጂአይ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች እና ወጣትና አንጋፋ ድምጻውያን ታድመዋል።

አውታር መልቲ ሚዲያ በሙዚቀኞች የተመሰረተ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሙዚቃ መሸጫ የስልክ መተግበሪያ ሲሆን በ2012 ዓ.ም ስራ መጀመሩ ይታወቃል። ለአድማጮች የሚፈልጉትን ሙዚቃ በቀላሉ፣ባፍጥነት እና በተመጣጣኝ ዋጋ ሲያቀርብ ለሙዚቃ ባለ ያውም የስራው ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያስችል ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *