ትናንትን አልደግምም

#ሰላም#EFDA#FIDEL

ባይነጋ ይመርጣል፣ እንደተኛ ሙቶ ቢገኝ ይመርጣል፡፡ አልጋው ላይ እንዳለ ወደ መቃብር ይዘውት ቢሄዱ ይመርጣል፣ አይኖቹ እንደተከደኑ ቢቀር ይመርጣል ፡፡ አይኖቹን መግለጥ እና ብርሃን ማየት ራሱ የሆነ የሚያስፈራ ነገር አለው፡፡በህይወት እንዳለ እንዳልሞተ እንኳን ለሌሎች ማሳወቅ ለራሱም ማሰብ አይፈልግም፡፡ ለነገሩ እንዳልሞተ ሰው የሚያስቆጥር ምን ነገር አለው? ልክ እንደለበሰው አንሶላ የጥፋተኝነት ስሜት ሰውነቱን ጠቅላላ ሸፍኖታል፡፡ያሳክከዋል፡፡ተነስቶ መታጠብ ይፈልጋል፡፡ሰውነትን በመታጠብ የቆሸሸ ነፍስን ማጽዳት ይቻላል ? ለራሱ ይጠይቃል ፡፡ ቢቻል ምነኛ መልካም ነበር ይላል ፤ እየራበው ነው ፡፡ በደመ ነፍስ አንሶላውን ወደ ጎን ገፋ አድርጎ ከመኝታው ተነሳ፡፡ እንደሁሌው እደሰሞኑ ደስታ የራቀው ሰውነቱን እየጎተተ ፊቱን ተለቃልቆ ቁርሱን ሊበላ ወጣ፡፡ቅርብ ያገኘው ካፌ ገብቶ አፉ ላይ የመጣለትን ምግብ አዞ ሳያጣጥም ሳይመዝን እያላመጠ የትናንት ብሩህ የፈኩ ቀኖቹን ማሰብ ጀመረ ፡፡ በሚበርድ አጉል የአፍላነት ትኩስ ያልተገራ ስሜት ተነድቶ ድንገት የናዳቸውን ብሩህ ቀኖቹን በምናቡ መሳል ጀመረ፡፡
ከወራት በፊት የዩንቨርስቲ ተማሪ ነበር፡፡
ከወራት በፊት የሚወደው ሰው ነበረው፡፡
ከወራት በፊት ብዙ ተስፋ ነበረው ፡፡
ከወራት በፊት የኔ የሚለው ብዙ ነገር ነበረው፡፡
ሁሉንም በራሱ ጥፋት ከመዳፉ ከመነጠቁ በፊት………..
እንዲህ አይነት ግንኙነት እና እንዲህ አይነት ልምምድ ውስጥ መቼ እንደገባ እንኳን ርግጠኛ አይደለም ፡፡ሁሉም ነገር እንደቀልድ የተጀመረ ነበር፡፡ በዩንቨርስቲው ስማቸው በበጎ ከማይነሳ ልጆች ጋር መዋልን እንደዘበት ነበር ማዘውተር የጀመረው፡፡ልክ ማግኔት በዙሪያው ያሉ ብረቶችን እንደሚስበው እና ራሱ ላይ እንደሚያጣብቀው ነበር የነሱም መሰባሰብ ፡፡ ቀስ በቀስ የክቡ የስብስቡ አስኳል ሆነ ፡፡ ሌሎች ግንኙነቶቹ ሸክም እንደበዛበት መረብ እየላሉ እየላሉ እየተበጣጠሱ መጡና ዙሪያው በዚህ ስብስብ ብቻ ታጠረ ፡፡ እነማን ይህንን ስብስብ እንደፈጠሩት በውል አያውቅም ፡፡ ግን ብቻ የሆነ ቀን ራሱን በነሱ ታጥሮ አግኝቶታል ፡፡ መውጣት አልቻለም፡፡ የሆነ የተመቸው ነገር አለ ፡፡ ምንድነው ቢሉት ግን ራሱ ማብራራት የማይችለው የሆነ ነገር አጣብቆ ይዞታል፡፡ ብዙውን ጊዜ አመሻሽ ላይ ከእኒህ አዳዲስ ወዳጆቹ ጋር ሻይ ለመጠጣት ከግቢ ይወጣል፡፡ አብረው ያመሻሉ ፤ አብረው ያድራሉ፡፡
ከእነዚህ ቀናት በአንዱ በሚማሩበት ዩንቨርስቲ እንደዘበት በሁለት ተማሪዎች መሃል መጠነኛ አለመግባባት ተፈጠረና ጉልበት ተፈታተሹ፡፡ ግጭቱ ግን በሁለቱ መሃል አላበቃም ፡፡ሌሎች ችግር መቼ በመጣ ብለው ክንብንባቸው ውስጥ አድፍጠው በሚጠብቁ የጸብ አጋፋሪዎች ጣልቃ መግባት ጠቡ የግል ሳይሆን የቡድን ገጽታን እየያዘ መጣ ፡ ማንም ነገሮችን ቆም ብሎ ለማየት ሰከን ብሎ ለመመርመር አልተዘጋጀም፡፡ ሁሉም በስሜት እየተነዳ የጥፋት ጭዳ ሆነ ፡፡ አብረዋቸው ፊደል እና እንጀራ የተቋደሱ ባልንጀሮቻቸው ላይ ድንጋይ እና ስለት አነሱ፡፡ ሚኪም የነገሮች ሁሉ ፊትአውራሪ ሁኖ ሰነበተ፡፡ከ 3 ቀን በኋላ ነገሮች እየተቀዛቀዙ መጡ ግን እንደቀድሟቸው መሆን አልቻሉም ፡፡ የማይመለሱ ቀናት የማይመለሱ ነገሮችን ይዘው ተሰውረዋል፡፡
ለአመታት የኖሩበትን ህይወት ለመኖር አይደለም ለሌሎች ለማስረዳት እንኳ የማይቻል ከባድ ህይወትን ተጋፍጠው እና አሸንፈው የዩንቨርስቲ በራፍን መርገጥ የቻሉ ፤ እርፍ ጨብጦ እየዋለ ዘውትር የልጆቹን ማዕረግ ከሚናፍቅ ምስኪን ገበሬ አባት እና ህመም ፣ድካም እና ረሃቧን ሁሉ በአንድ መቀነት አጥብቃ አስራ ደፋ ቀና እያለች የልጇቿን ወግ ከምትጠብቅ ምስኪን እናት የተወለዱ አራት ተማሪዎች አስክሬን እንደዘበት በሳጥን ተሸክፎ ወደ መጡበት ቀዬ ተሸኘ፡፡ የአካባቢው ሆስፒታሎች በቁስለኛ ተማሪዎች ተሞሉ፡፡ህይወት በትልቁ ከሰረች …..ግን ማንም ምንም አላተረፈም ነበር ፡፡
ሚኪም የጸቡ አስተባባሪ ነበርና በፖሊስ ተይዞ እስር ቤት ገባ ፡፡ ከወራት በኋላ ግን እስር ቤት ውስጥ ሁኖ የሆነውን የተፈጠረውን ነገር ማሰብ መለስ ብለሎ በሰከነ መንፈስ መመርመር ጀመረ ፡፡ መታለሉ ፣ ባልገባው እና በማያገባው ነገር ውስጥ ገብቶ እንደነበር እየተገለጠለት መጣ ፡፡ገለባ ሁኖ ነበር ፡፡ ልቡ እንደገለባ ሁኖ ነበር ፡፡ ገለባ ነፋስ ወዳሻው ስፍራ እንደሚነዳው ሁሉ እሱም በሌሎች እየተነዳ ነበር ፡፡ አሁን ነው ሁሉም ነገር የገባው ፡፡ ግን ምን ማድረግ ይችላል ? የነበረውን እንዳልነበር ማድረግ ይችላል? አይችልም ፡፡ ረፍዶበታል፡፡ ከት/ ቤቱ ተባሯል፤ ከፍቅረኛው ተለያይቷል ፤የአመታት ልፋቱን ሁሉ በራሱ እጅ አንቆ ገድሏል ፡፡ ካጣው ከተነጠቀው ነገር በላይ ደግሞ የበለጠ ያንገበገበው ደግሞ የሰዎች መጠቀሚያ መረማመጃ ድልድይ መሆኑ ነበር ፤አሁን ነው የገባው ፡፡ግራ ቀኝ ፊትና ኋላ ከበውት በአጉል ውዳሴ አጀግነውት የአላማቸው ማሳኪያ የኢላማቸው መምቻ ጠጠር እንዳደረጉት ዘግይቶ ነው የተገለጠለት ፡፡
ዛሬ ሚኪ የእርምት ጊዜውን ጨርሶ ከማረሚያ ቤት ወጥቷል፡፡ ግን ባዶ እጁን አልነበረም የወጣው ፣ በጸጸት የተሞላ ልቡን፣ በድብርት የተጎሳቆለ ሰውነቱን እና በተስፋ መቁረጥ የዛለ ማንነቱን ይዞ ነበር ፤ ባዶ ሁኖ ነበር ፤ባዶ፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡ ልክ ከዚህ ቀጥሎ እንዳለው ቦታ

ይህንን ባዶነት ተሸክሞ ለወራት እየናወዘ ነው ፡፡ ትናንቶቹ ከዛሬ የተለዩ አልነበሩም ፡፡ ዛሬም ያው በተለመደው ሰላም አልባ ቀን ላይ ተቀምጦ ነገን በትዝታ ያላምጣል ፡፡ የራሱን ህይወት ብቻ አልነበረም ያበላሸው ፡፡ የሌሎች የሱ ቢጤ እኩዮቹን ብርሃን ነበር ያጨለመው ፡፡ለልጇ ምርቃት ሰስታ ባስቀመጠችው ጥሪት እናት የልጇን አርባ እንድታወጣ አድርጓል፡፡ ልጄ ሲመረቅ እለብሰዋለው ብለው ሰስተው ያስቀመጡትን ልብስ ሽጠው አባት የልጃቸውን ፍትሃት እንዲከፍሉ አድርጓል፡፡ እዚህ ውስጥ እጁ እንዳለበት ሲያስብ ራሱን ይጠላዋል፡፡
ይህ ታሪክ እሱ የሚማርበት የነበረው ዩንቨርስቲ ታሪክ ብቻ አልነበረም ፡፡በአብዛኞቹ የሃገራችን የትምህር ተቋማት ውስጥ የተፈጠረ አሳዛኝም አሳፋሪም ታሪክ ነው ፡፡፡
እያደር ሚኪም ነገሮችን እያጤነ እያገናዘበ ያበላሸውን ህይወት ተቀምጦ ጸጸት ባማላመጥ መቀየር እንደማይችል………….. ግን ግን የሰበረውን ህይወት መጠገን ባይችልም ሌሎች የእሱን ታሪክ እንዳይደግሙት ማድረግ እንደሚችል ማሰብ ጀመረ፡፡
በቀላሉ ከሚያውቃቸው ጓደኞቹ መጀመር ይችላል ፡፡ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት አብረውት ከተማሩት እና አሁን በተለያዩ ዩንቨርስቲዎች ከሚማሩት ልጆች ጋር በማህበራዊ ሚዲያ ይገናኛሉ ፡፡ ስለሚማሩበት ዩንቨርስቲ፣ ስላሳላፉት ህይወት ፣ የሃይስኩል ላይፍ………….. ያወራሉ ፡፡እናም ይህንን መልካም አጋጣሚ መጠቀም እንደሚችል አሰበ ፡፡ ሰላም የሚል የቴሌግራም ቻናል እና የፌስቡክ ገጽ ከፍቶ ጓደኞቹን ጠቅላላ ለአባልነት ጋበዘ ፤ እነሱም ሌሎችን እንዲጋብዙ ጥሪ አቀረበ ፡፡ እንዲህ እንዲህ እያደረገ ከ 12000 በላይ ተማሪዎች አባል የሆኑበት ቡድን መሰረተ ፡፡ አሁን በዚህ የቴሌግራም ቻናል ሰላም አብዝቶ ይሰበክበታል ፤ ዘረኝነት እና ጽንፈኝነት ይነቀፍበታል፡፡ ሁሉም አባላት ስለሚማሩበት ዩንቨርስቲ ሰላም እና አብረዋቸው ስለሚማሩ ተማሪዎች ደህንነት ይመክራሉ ፤ከተመረቁ በኋላ ስራ ፈጥረው መስራት ስለሚችሉባቸው የስራ እና ገቢ ማግኛ መንገዶች ይወያያሉ ፡፡ በአካባቢያቸው የሚገኙ እና ስራ አጥ የሆኑ ወጣቶች እንዴት ስራ መስራት እንደሚችሉ ይመክራሉ ፡፡ በየፌስቡክ ገጾቻቸው የሰላምን መዝሙር ይተይባሉ ፤ ያስነብባሉ ፡፡ አሁን ሚኪ በየዕለቱ ሰላምን ለተማሪዎች የሚሰብክ የሰላም አምባሳደር ሁኗል ፡፡
ትምህርት ለልማት ማህበር ወጣቶችን ወደ ሰላም አውድ ለማምጣት የሚሰራ ሃገር በቀል ድርጅት ነው ፡፡የመንግስት ሃላፊዎችን ከወጣቶች ጋር በማቀራረብ የማወያየት ስራን እየሰራ ነው ፡፡ በወለጋ ጊምቢ፣ነጆ እና ቅልጡ ካራ ወረዳዎችም ላይ ከ120 በላይ ወጣቶችን እና የመንግስት የስራ ሃላፊዎችን ስለሰላም አወያይቷል ፡፡ ተሳታፊዎች ተቀራርበው እንዲሰሩ ድልድይ ሁኗል፡፡
ስለ ሰላም መስበክ ፣ስለሰላም መዘመር ፣ ለሰላም ዘብ መቆም የሁላችን የቤት ስራ ነውና ሁላችን እጅ በእጅ ተያይዘን ስለ ሰላም እንቁም ፣ ሰላም ለሁላችን ፣ሰላም ለሃገራችን ይሁን !!!!
ይህ መልዕክት የተላለፈላችሁ በትምህርት ለልማት ማህበር (Education For Development Association) ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *