በአማኑኤል ሆስፒታል ተመላላሽ የአዕምሮ ህመም ታካሚው ሰው ቁጥር በቀን እስከ 500 ደርሷል

በኢትዮጵያ ብዙም ትኩረት ያልተሰጠው የአእምሮ መቃወስ ወይንም ህመም ቁጥሩ በፍጥነት አየጨመረ የመጣ ሲሆን መርካቶን አለፍ ብሎ በሚገኘው በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ስር የሚተዳደረው የአማኑኤል አዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በቀን በአማካኝ ከ450 እሰከ 500 ተመላላሽ ታካሚዎችን እያከመ መሆኑን ፊደል ፖሰት ከሆስፒታሉ ያገኘው መረጃ ያሳያል።

ከሰማንያ አራት አመት በፊት የተገነባው ይሄ ሆስፒታል 235 አልጎች አልጋ ያለው ሲሆን በአሁኑ ሰአት አልጋ ሞልቶ ወደ 120 የሚጠጉ ከባድ የአእምሮ ህመም ታማሚዎች ህክምና ለማግኘት አልጋ እየተጠባበቁ እንደሚገኙም ተገልፇል ።

በተመላላሽም ሆነ አልጋ ይዘው ከሚታከሙት ውስጥ አብዛኞቹ የእዕምሮ ህመም ታማሚዎች ከ20 አስከ 40 ባለው እድሜ ውስጥ የሚገኙ ናቸው።
የአብዛኞቹ ታካሚዎች የህመም አይነት ከባድ የአእምሮ ህመም/ psychosis ውስጥ የሚመደብ ሲሆን ይሄም የተሳሳተ ሀሳብ ውስጥ መዘፈቅ ፣መዘላበድ ፣ እየተደረገ ስላለው እውነታ የተሳሳተ ግንዛቤ መኖር፣አንድን ሰው ሌላ ሰው እንደሆነ አድርጎ ማየት አንዲሁም ሌላ ሰው የማይሰማውን ድምፅ መስማት ከህመማቸው መገለጫዎች ጥቂቶቹ ናቸው።

ድባቴ ፣ የጭንቀት ህመም ፣በአድንዛዥ እፅ ሱስ ሳቢያ የሚመጣ የአዕምሮ ህመም በሆስፒታሉ ከሚታከሙት ሰዎች መሀል የሚታይባቸው ምልክት ነው።
አንደ ስነ ልቦና ባለሞያዎች ከሆነ በሀገሪቱ ያለው የማህበራዊ ፣የፖለቲካ ፣የጤና ፣የስነ ልቦና ፣የሰላም እጦት ፣የአደንዛዥ እፅና የመጠጥ ሱስ ተጠቂ ቁጥር መጨመር ብዙ ኢትዮያውያንን ለአእምሮ ህመም እየዳረገ መሆኑን ያነሳሉ።

በየካቲት ወር 2009 ዓ.ም. በሆስፒታሉ ስር ሆኖ  የየካ ኮተቤ ሆስፒታል የአዕምሮ ህክምና ቢጀምርም ለኮሮና ህክምና መዋሉ በአማኑኤል ሆስፒታል የስራ ጫናን እንደፈጠረ የሆስፒታሉ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ አብዪ የኔ አለም ለፊደል ፖስት ገልፀዋል።
” ከሁሉም የሀገሪቱ ክልል የሚመጣ ታማሚ ነው እዚ የምናስተናግደው ። የታማሚ ቁጥር በየአመቱ እየጨመረ ነው ። ችግሩን ለመቅረፍ በርከት ያሉ ሆስፒታሎች ፣በርከት ያሉ የሥነ ልቦና ሐኪሞች ማቅረብ ይኖርብናል ” ብለዋል።

በወር አስከ 10,000 ተመላላሽ ታካሚ በሚያስተናግደው በአማኑኤል ሆስፒታል 12 ስፔሻል የሥነ ልቦና ሐኪም ብቻ ነው ያለው ። በሆስፒታሉ አልጋ ይዞ ለሚታከም ታማሚ በመንግስት የተመደበው የቀን የምግብ ወጪ 18 ብር ሲሆን ምግቡንም በጨረታ አሸንፈው የገቡ ምግብ ቤቶች ያቀርባሉ።
ሆስፖታሉ ሲገነባ ፀጥ ያለ ስፍራ ላይ የነበረ ቢሆንም ከአዲስ አበባ ህዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ ቦታው ከውጪ ቅልጥ ያለ የገበያ መንደር ያለበት ሆኗል።

አልጋ ይዘው ከሚታከሙት ታማሚዎች መሀከል የጊቢውን አጥር ዘሎ ለመውጣትና ለማምለጥ መሞከር በተደጋጋሚ የሚያጋጥሙ ችግሮች ናቸው።
ሆስፒታል ውስጥ 13 የበሽተኛ ዋርዶች( የበሽተኛ የመኝታ ከፍሎችን የያዘ ሰፋ ያለ ቤት) ከዚህ ውስጥ አንዱ ዋርድ በሱስ ለተጠቁ ታማሚዎች የመኝታ ክፍል ሆኖ ያገለግላል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *