በሸገር የምትራመዱበት ጫማ የእናንተ ነው ።መንገዱ ግን የታታሪው ኢንጂነር ፍቃደ ነው።

103 የመንገድ እና 15 የኮብልስቶን ንጣፍ ፕሮጀክቶች ላይ የደከመ ጀግና! !!!

የኢትዪጵያ ብሔራዊ ቡድን ኳስ ሲጫወት በስሜት ቁጭ ብድግ እያሉ የሚያዩት እንጂነር ፍቃደ ሀይሌ ለአዲስ አመት ደህና ነበሩ ። የጓደኞቻቸውን ስልክ እያነሱ ደህና ነኝ ብለዋል ። በሞባይላቸው ለሚደርሳቸው የእንኳን አደረስዎ መልእክት ምላሽ ሰጥተዋል ።

ትናንት እሁድ ከሰአት የሞት ዜናቸው ከመሰማቱ በፊት የነበሩ አምሰት ቀናት ግን አስጨናቂዎች ነበሩ ። ያ በአዲስ አበባ በ14 አመት ውስጥ ከ1,000 ኪሎ ሜትር በላይ መንገድ የዘረጋ ብልህ አእምሮ ፣ በአዲስ አበበ መንደሮች በተነጠፉ የኮብልስቶን መንገድ ላይ ክንዴ ዛለ ሳይል የተሳተፈ ሰው፣ በኤርትራ በሀኒሽ ደሴት ኤርፖር ግንባታ፣ ፣በደርግ የአዲግራት መንገድ ፕሮጀክት ፅ/ ቤት ሀላፊ ፣በአውራ ጎዳና ፕሮጀክቶች 20 አመት የሰራ ጎልበት ብዙ ወዳጅ ያሳጣን ኮሮና ኢንጅነራችን አሳጥቶናል።


ኢንጅነር ፍቃደ በኮሮና እንደተያዙ ወደ ዘውዲቱ ሆስፒታል አመሩ ።ከዛም ወደ ሚልንየም አዳራሽ አመሩ ። ኮሮናቫይረስ ትንፋሽ አሳጥቶ ጀግናችንን በአምሰት ቀን ውስጥ ለሞት እጅ እንዲሰጡ አደረገ ። ሞት ጨካኝ ነው! !!
ኢንጂነሩ የቆየ የስኳር በሽታ ይኖርባቸው እንጂ አልጋ ላይ የሚያሰተኛ ህመም እንዳልነበራቸው የቅርብ ጓደኞቻቸው ለፊደል ፖስት ገልፀዋል።
በቋንቋ ረገድ ከአማራኛ ውጪ እንግሊዘኛ አቀላጥፈው ይናገሩ ነበር ። ጉራገኛ ና ኦሮመኛ ይሰማሉ ይናገራሉ።

ሐምሌ 1 ቀን 1953 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ፍለውሃ ኦርማ ገራዥ የተወለዱት ኢንጅነር ፍቃደ ቤተሰቦቹ በአነስተኛ ገቢ የሚተዳደሩ የነበሩ በመሆናቸው መሰረታዊውን ትምህርት ለማግኘት በጣም ይቸገሩ ነበር ፡፡ ለትምህርት ያለቸው ፍላጎት ከፍተኛ በመሆኑ የአባታቸው ታናሽ ወንድም አቶ ሓይሌ ሶዶን በራሱ ተነሳሽነት በመጠየቅ እሳቸውም የተማሩ በመሆናቸው የግል ትምህርት ቤት ከፍለው ከ1ኛ እስከ 4ኛ ክፍል በሁዋላም በጉዋደኛቸው አማካይነት የመንግሥት ት/ቤት ተማሪ በማድረግ እሰከ ዩንቨርሲቲ ድረስ ትምህርታቸው እነድዲያጠናቅቁ አርገዋቸዋል።
ወጣቱ ፍቃዱ ለትምህርት ካለው ከፍተኛ ፍቅር የተነሳ ትምህርቱን ሌት ከቀን በማጥናት በከፍተኛ ውጤት በአብዛኛው ከክፍሉና ከትምህርት ቤቱ አንደኛ በመውጣትና በሶስቱም ብሄራዊ ፈተናዎች በእጅግ ከፍተኛ ማዕረግ በማለፍ
የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ከ1ኛ እስከ 4ኛ ክፍል በ2 ዓመት( 1958 ና 1959 ዓ.ም.) በተስፋ ትምህርት ቤት ቦሌ ወሎ ሰፈር ፣ ከ5ኛ እሰከ 8ኛ ክፍል በፊታውራሪ ላቀ አድገህ ትምህርት ቤት (1960 እስከ 1964 ዓ.ም.)
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት በሽመልስ ሀብቴ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት 9ኛ ና 10ኛ ክፍል በዳግማዊ ምንሊክ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት 11ኛና 12ኛ ክፍል ከ 1965 ዓ.ም. እስከ 1971 ዓ.ም. ( የእድገት በህብረትና የዕውቀትና የሥራ ዘመቻ ተሳታፊ በመሆን ከ1967 ዓ.ም. 1968 ዓ.ም. መጨረሻ የዘመቻ ግዳጁን በመማጠናቀቅ ሰርተፊኬት ተሰጥቶታል።

በቢኤስ ሲ ዲገሪ በሲቪል ምህንድስና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኢትዮጵያ 1975 ዓ.ም. ተመርቋል።

በአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን በቆዩባቸው 14 አመታት የጎተራ ማሰለጫ ፣ ከአውቶብስ ተራ እስከ አትክልት ተራ፣ ከአራት ኪሎ -ቀበና እስከ መገናኛ ፣ከሀይሌ ጋርመንት እሰከ አቃቂ ፣አዲሱ የቦሌ መንገድ ፣ከአብነት እስከ ልደታ ፍርድ ቤት ፣በባቡር ሀዲዶች ጎን ጎን ያሉት መንገዶች ፣በአዲስ አበባ የተነጠፉት ኮብልስቶን መንገዶች ፣በኮንዲሚንየም አካባቢ የተዘረጉ አስፋልቶች ከብዙ በጥቂቱ በኢንጅነሩ አመራርነት የተሰሩ መንገዶች ናቸው።

አዲስ አበባ ቀላል ባቡር ጥንስስ ጽ/ቤትን በአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ውስጥ በቅድሚያ በማቐቐም በመቀጠልም የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ሲቐቐም ጽ/ቤቱን እንዲዛወር ማድረግና የኮርፖሬሽኑ የቦርድ አባልና የቦርዱ የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ በመሆንና የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጄክትን የመንገድና የባቡር መሰረተ ልማት በቅንጅት በመምራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ የመጀመሪያው የአዲስ አበባ ቀላል ባቡርና የኢትዮጂቡቲን ዋና ባቡር በማስጀመር ታሪካዊ አሻራውቸውን አስቀምጡዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ የመንገድ አቅጣጫ ስያሜ አመልካች ዘመናዊ ምሰሶዎችን በሌላው ዓለም ያለውን ተሞክሮ በመውሰድ ከቀለበት መንገዱ በመጀመር ሁሉም የከተማዋ መንገዶች እንዲኖራቸው በማድረግ ለከተማችን መሰረት ጥለዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣንን የ 15 ዓመት የመንገድ ልማት ፕሮግራም በ1996 ዓ.ም. በመቅረጽ የከተማዋን ዋና ዋና መንገዶች፣ የውስጥ ለውስጥ መንገዶችንና ዘመናዊ የከተማ መንገዶች ዲዛይን፣ ቁጥጥርና ኮንትራት አስተዳደር ፕሮጄክቶች በመምራት ያለውን እውቀትና ልምድ በ ማበርከት ከተማውን የመንገድ አውታር በ1995 ዓ.ም ሲረከብ ከነበረበት 1500 ኪሎ ሜትር 6000 ኪሎ ሜትር በ14 ዓመታት ሃላፊነቱ እንዲደርስ ያደረገ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ የሚከተሉትን ብርቅዬ የከተማችን መንገዶች በመገንባትና በማስገንባት አሻራውን አኑርዋል ።

አሁን እየተሰሩ ያሉት ከቃሊቲ ማሰልጠኛ እሰከ ቱሉ ዲምቱ እንዱሁም ከአውቶብስ ተራ እስከ ፑሽኪን አዳባባይ ያሉ መንገዶች የኢንጅነሩ ንድፎች ናቸው።
በአቶ አርከበ እቁባይ ( የጠ/ ሚ አብይ አህመድ አማካሪ) በቀድሞ የኢትዮጵያ ጠ/ ሚ መለስ ዜናዊ ሀሳብ ወደ አዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን የመጡት ኢንጅነር ፍቃደ እጅግ ታታሪ ተብሎ ከሚመደብ ሰው ውስጥ የሚመደቡ ናቸው።
እንደውም አንዴ አቶ መለስ ያሉበት ቤተ መንግስት ጎራ ሲሉ የጊቢው መንገድ ብዙ ቦታ ተቦርድሶ ሶያዩት” ምነው ክቡር ጠ/ ሚ እንግዳ የሚቀበሉበት መንገድ እንደዚህ እንዴት ይሆናል? ” ብለው አቶ መለስ በጀት በመንግስት እንዲያስዙ አርገው መንገዱን እንዳሰሩት ይነገራል።
“የፕሮጀክቶች ሀላፊ ብዙ እንቅልፍ ” መተኛት የለበትም የሚል ብሂል አላቸው ። ለሊት 11 ሰአት ተነስተው በአዲስ የሚሰሩ መንገዶችን በመኪናቸው ተዛውረው ካዩ በኋላ ሁለት ሰአት ቢሯቸው ይገኛሉ ።
አዲስ አበበ መንገዶች ባለ ስልጣን እየሰሩ የአመት የእረፍት ፍቃድ ወስደው አያውቁም ።አስፈላጊ ከሆነ እስከ እኩለ ለሊት ቢሮ ያመሻሉ ። ከቤተሰብም ጋር ” ለስራ እንጂ ለቤተሰብ ግዜ አትሰጥም ” ተብለው ብዙ ግዜ ወቀሳ ይደርስባቸው ነበር።

።” ለነገ የሚባል ስራ የለም ” በሚባል አቋማቸው የሚታወቁ ሲሆን አዲስ አበባን መንገድ የጎግል ካርታ እንኳን እንደሳቸው አያውቀውም ። ቢሮ ካሉት የስራ ባልደረቦቻቸው ጋር አንድን ፕሮጀክት በጥልቅ ሲያስረዱ የዩንቨርስቲ ሌክቸር ነው ሚመስለው ።
የቀን ሰራተኛ ሆነ የቢሮ ሰራተኛ ኢንጅነሩ ጋር እኩል ነው ።የሰራተኞች ግብዣ ሲኖር እኩል እታች ካለው ሰራተኛ ጋር ስራ በማገዝ ውር ውር ይላሉ ። ወጥ የሚሰሩ ሰራተኞች ጋር ሄደው ” እረ ራበን ይፍጠን እንጂ ብለው” ቀልደው ይመለሳሉ ።ስራ ላይ ግን ቀልድ የለም ።
አንዴ እኩለ ለሊት ላይ ሳር ቤት የሚገኘው ዋና መስሪያ ቤታቸው ከተፍ ብለው መኪና ክላክስ ሲያደርጉ ጥበቆቹ መሳሪያ ይዘው ማነው ብለው ሲመጡ ” ጎበዝ እንዲህ ነቅታችሁ ” ጠብቁ ብለው መመለሳቸው አሁንም ድረስ በመስሪያቤታቸው ይወራል።
ሱፍ ልብስ የሚያዘወትሩትና ለክትፎ መመገብ የሚወዱት ኢንጀነር ፍቃደ ከተራ መሃንዲስነት በመጀመር ደረጃ በደረጃ በፕሮጄክቶች ተጠሪ መሃንዲስነት፣ በፕሮጄክቶች ሥራ አሥኪያጅነት ፤ በመንገድ ጥገና አገር አቀፍ ዲስትሪክት ሥራ አሥኪያጅነት ፣በኢትዮጵያ መንገዶች ባለ ስልጣን (በኢመባ) ዋናው መሃንዲስ ቢሮ በከፍተኛ የቢሮ መሃንዲስነት፣ በኢመባ ዋና መሃንዲስነትና ምክትል ሥራ አሥኪያጅነት ፣ በኢመባ ዋና ሥራ አሥኪያጅ የቴክኒክ ዋና አማካሪነት፣ የመጀመሪያው የኢመባ የመንገድ ልማት ፕሮግራም አስተባባሪነት፣ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ሥራ አሥኪያጅ በመሆን ባለማቐረጥ በተከታታይ ከ አራት የከተማችን ከንቲቦች ጋር ( ከአቶ አርከበ ዑቅባይ፤ ከአቶ ብርሃነ ደሬሳ፤ ከአቶ ኩማ ደምቅሳና ከአቶ ድሪባ ኩማ ) ና በምክትል ቢሮ ሃላፊነት ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ የአቶ ድሪባ ኩማ የቴክኒክ አማካሪ በመሆን ከማገልገሉም በላይ በነዚህ ጊዚያት ውስጥ ከነዚህ ሃላፊነቶች በተጨማሪ ከ 10 በላይ የሆኑ መሥሪያ ቤቶች የቦርድ ሰብሳቢና አባል በመሆን ከፍተኛ አገልግሎት አበርክቱዋል፡፡

ኢነጂነር ፍቃዱ ሃይሌ ለሙያው ካለው ከፍተኛ ፍቅርና ክብር የተነሳ በሌለው ጊዜ የኢትዮጵያ ሲቪል መሃንዲሶች አባል ፣ አመራርና በመጨረሻ ፕሬዚደንት በመሆን ለ 6 ዓመታት በማገልገል በማህበሩ የሚሰጠው ከፍተኛ የሲቪል ምህንድስና የአገልግሎት መጠሪያ የፌሎ ኢንጂነር ስም ተሰጥቶታል፡ኢንጂነር ፍቃዱ ሃይሌ ከ መጋቢት ወር 2012 ዓ.ም ጀምሮ ከመንግሥት ስራና ሃላፊነት በጡረታ ተገልሎ በግል አማካሪነት በመሥራት ላይ ይገኙ ነበር።
ኢንጅነሩ ከሙስና ጋር በተያያዘ 46 ክሶች ቢቀርብባቸውም 45 ወድቅ ሆነው በአንዱ ብቻ ተከሰው እሱም ክሱ ተቋርጦ ከአመት በፊት ከእስር ተፈተዋል ። ከዚያ በኋላ ወደ ስራ ተመለሱ ቢባሉም “አሰናብቱኝ “በማለታቸው በጡረታ ተሰናብተዋል።

የተሳካ የትዳር ሒወት የነበራቸው ኢንጂነር ፍቃደ ሃይሌ በ1978 ዓም አብሮ አደጉ ከሆነችው ከመምህርት ወ/ሮ በቀለች ተፈራ ጋር ህጋዊ ጋብቻውን በመፈጸም 4 ወንዶችና 3 ሴት ልጆች በማፍራት ትልቅ ቤተሰብ በመመሥረት ከባለቤቱ ጋር በተደረገ የተሳካ ሃላፊነት በመወጣት ልጆቻቸው የሆኑት አንተነህ ፍቃዱ ሃይሌ (ኢኮኖሚስት)፣ ፍጹም ፍቃዱ ሃይሌ (ሲቪል መሃንዲስ)
፣ቤዛዊት ፍቃዱ ሃይሌ (ሲቪለ መሃንዲስ)፣ ፍሬህይወት ፍቃዱ ሃይሌ (የህክምናዶክተር) ሆነዋል ። እንዲሁም ቢኒያም ፍቃዱ ሃይሌ ሲቪል ምህንድስና ፣ ሰላማዊት ቃዱ ሃይሌ ሕክምና ፣ምንያህል ፍቃዱ ሃይሌ ኮምፒውተር ኢነጂነሪንግ በመማር ላይ ይገኛሉ።

የሚሌ አሰብ መንገድ ፕሮጄክት ሥራ አሥኪያጅ ሆነው በተደራቢነት የ አሰብ የተዋጊ ሄሊኮፕተሮች ማረፊያ የኮንክሪት አስፋልት ግንባታ ፕሮጄክት ( 300 ሜትር በ 90 ሜትር ) ሥራ አሥኪያጅ እንዲሁም የመቀሌን፤ የጎንደርንና የላሊበላ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ሥራዎች አስጀምረዋል።

ከታህሳስ 1982 – ግንቦት 1983 ዓ.ም. ደግሞ
በኢመባ የዳህላክ የአውሮፕላን ማረፊያ (3000 ሜትር በ 45ሜትር) ግንባታ ዋና ሥራ አሥኪያጅ ሆነውም አገልግለዋል።
የኢትዮጵያ ሰራተኛ አሰሪ ፊዴሬሽን ሀምሳኛ አመት ሲያከበር በምርጥ አመራርነት የተሸለሙ ሲሆን ከአርባ ሰባት በላይ የምስጋና እና የእውቅና ሽልማቶችና ሰርተክፌቶች አግኝተዋል።

ጀግና ስጋው አፈር ቢበላውም ስሙ ከመቃብር በላይ ነው።ኢንጅነር ፍቃደም ስማቸው ሲታወስ ይኖራል። መንገድ እንደገነቡልን እኛም በስማቸው መንገድ ገንብተን ማስታወስ አለብን! !!!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *