በሳፋሪኮም በጥሪ ማዕከል የሚሰሩ ኢትዮጵያኖች መከፈል ከሚገባን 65 % ደሞዛችን ተቆርጦ ነው የሚሰጠን ሲሉ የስራ አድማ አደረጉ
በአዲስ አበባ ልደታ የሚገኘው የሳፋሪ ኮም የጥሪ ማዕከል ሰራተኞች ትናንት እና ከትናንት በስቲያ ከደሞዝና ብልሹ አሰራር ጋር በተያያዘ የስራ አድማ አድረገዋል።
“አምሽተን ትራንስፖርት እየቀረበልን አይደለም ። በሳፋሪኮም በሌላ ሀገር የሚሰሩ የጥሪ ማዕከል ሰራተኞች ወደ ኢትዮጵያ ብር ሲመነዘር ከ24,000 _ 28,000 ብር እየተሰጣቸው እዚ ሀገር የትራንስፖርትና የቤት አበልን ጨምሮ ከ4,500 ብር በታች ነው እየተከፈለን ያለው ፣ የሒወት ኢንሹራንስ የለንም በማለት የጥሪ ማዕከሉን በሚያስተዳድረው ድርጅት (ISON Xperience) የወቀሱ ሲሆን ከሁለት ቀን የስራ አድማ በኋላ ወደ ስራ ተመልሰዋል።
ሰራተኞቹ የትራንስፖርት ተብሎ የሚሰጠን በወር 800 ብር ሲሆን ይሄም በቀን ሲሰላ ከ 27 ብር በታች መሆኑን ገልፀዋል።
ዋና ደሞዛቸው 3,300 ብር መሆኑን ገልፀው ይሄም ደሞዝ አንድ ዓለም አቀፍ ኩባንያ ውስጥ የሚሰራ ዲግሪ ያለው ሰው የሚከፈለው ደሞዝ አይደለም ብለዋል።
ሳፋሪኮም በበኩሉ በደሞዝ ጭማሪው ላይ መልስ መሰጠት ተቆጥቦ በጉዳዩ ላይ ለፊደል ፖሰት ይሄንን ምላሽ ሰጥቷል;
“የጥሪ ማዕከላችንን በሚያስተዳድረው ድርጅት (ISON Xperience) እና በሠራተኞቹ መካከል የተፈጠሩ አለመግባባቶች እንደነበሩ እናውቃለን።
ከድርጅቱ በተሰጠን መረጃ በሥራ አስፈጻሚዎችና ሠራተኞች መካከል የተፈጠረው የአለመግባባት ተፈትቶ መደበኛ የሥራ እንቅስቃሴዎች እንደቀጠሉ ተረድተናል።
በዚህ ወቅት በደንበኞች አገልግሎት ላይ ምንም ዓይነት መስተጓጎል እንዳይፈጠር እና ደንበኞች እንደቀድሞው እንዲስተናገዱ አስፈላጊው ዝግጅቶች ተደርገው ነበር”