ሱሊማኒ ለኢራን ህብረት እንዳመጣ የህዳሴ ግድብ ህመም ለኢትዮጵያ አንድነት ያስገኝ ይሆን?

በተስፋዬ ጌትነት

በዚህ አመት ህዳር ላይ በነዳጅ ዋጋ ንረት በተነሳ ተቃውሞ የኢስላሚክ ሪፐብሊኩ የኢራን መንግስት ችግር ውስጥ ወድቆ ነበር ። የሀገሪቱ መንፈሳዊ መሪ አያቶላ ካህምኒ ለፀጥታ አካሎቻቸው ” አስፈላጊ የሆነ እርምጃ ውሰዱ” በማለታቸው ከ600 በላይ ዜጎች ሞተው ከሺ በላይ ዜጎች ቁስለዋል ።በህዝቡም መካከል የመንግሰት እና የተቃዋሚ ጎራ መከፋፈል ተጀምሮ ከ40 አመት በላይ ግጭት ያላስተናገደችውን ኢራንን ወደ ጦርነት ሊጋብዝ ጫፍ ደርሶ ነበር ።
ነገር ግን በታህሳስ መጨረሻ ኢራቅ ርዕሰ መዲና በባግዳድ ግዳጅ ውስጥ የነበረው ጄኔራል ቃሲም ሱሉማኒ በአሜሪካ አየር ጥቃት ሲገደል ሁሉም ኢራናዊያን አንድ ሆኑ ።የጄኔራሉ ሞትም የውስጥ ችግራቸውን ለጊዜው ተወት አርገው በሀገር አንድነት እንዲመካከሩ የውጭ ጠላታቸውን ለመመከት እንዲመካከሩ እድል ሰጥቷቸዋል ።
ወደ ኢትዮጰያ ስንመጣ በኦሮሞ አክቲቭስትነቱና ፓለቲከኝነቱ የሚታወቀው እንዲሁም የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን መንግስትን ” አህዳዊነት ለመመስረት ነው የሚሰራው የብሔር መብትን ገሸሸ ያረጋል ” ብሎ የሚሟገተው ጃዋር መሀመድ አሜሪካ በህዳሴ ግድብ አሞላል ላይ ኢትዮጵያ ግብፅንና ሱዳንን ስምምነት ጋር ሳታደርግ ግድቡን ዉሀ መሙላት የሚለውን አቋሟን ከመንግስት ቀድሞ የተቃወመ የመጀመርያው ፓለቲከኛ ነው ።በፌስ ቡኩ ከ3,300 በላይ ተከታዮቹ በተጋሩለት በእንግሊዘኛ የተፃፈው ፅሁፊ በአጭሩ እንዲህ ይላል” የአሜሪካ ትእዛዝ የቀኝ ግዛት አመለካከት ነው ። የአፍሪካ ሀገራትም አይቀበሉትም ።ኢትዮጵያን ባለመነችበት ነገር እንድትፈርም ማድረግ አግባብም ህጋዊም አይደለም ።መጪውን ትውልድ ጥቅምም ይጋፋል። መጪውን ምርጫና እንኩ ያሉንን ብድር በማማከኘት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ጫና አየተደረገ ነው ።ጠ/ ሚኒስተሩ አሜሪካን ታዛቢ ሲያረግ ተሳስቷል ።ሆኖም ግን የስምምነት ፊርማ ባለመፈረሙ መልካም ስራ ሰርቷል።በዚህ ሁላቹንም ከጎኑ ልንቆም ይገባል ።ጉዳዮን ወደ አፍሪካ ህብረት ወስዶ መደራደርም ይገባል ” ሲል ጃዋር ፅሁፉን አስፍሯል።
ከጃዋር የፌስ ቡክ ፅሁፍ ላይ ተመርኩዛ አንዲት ሰናይት የተባለች ተከታዮ እንዲህ ስትል አስተያየቷን አስፍራለች
“ጃዋር አሁን በጣም አስደስተኽኛል:: የፈለገ ብንናቆር የውጭ ጠላት ሲመጣ አብረን መመከት ልማዳችን ነው:: ለመፋቀርም ለመጣላትም አግር ሲኖር ነውና” በማለት የጃዋርን ፅሁፍ ከኢትዮጵያ አንድነት ጋር አያይዘዋለች ።
መቀሌ የሚገኙት ከጠ/ ሚኒስትሩ ጋር ያላቸው ግንኙነት ሞቅ ቀዝቀዝ የሚለው ፓርቲያቸው ህውሃት የአቶ አብይን ብልፅግና ያልተቀላቀለው የትግራይ ክልል ም/ል ርዕሰ መስተዳደር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል አድዋ በተከበረው 124 የአድዋ ድል በአል ላይ ባስተላለፉት መልእክት
“ሰሞኑን የህዳሴው ግድብን አስመልክቶ የቀረበው የውል ሰነድ ቆም ብለን ከውጫሌው ውል በመማር በውሉ የሰፈሩ ሓሳቦችና ቃላቶች በሉኣላዊነታችን ላይ የመጡ ከዛም አልፎ ለሌላ ጂኦፖለቲካዊ ዓላማ ማስፈፀሚያ ገፀ በረከትና እጅ መንሻ ሆኖ እንዳያገለግል በከፍተኛ ጥንቃቄና ሓላፊነት መፈፀም ይገባል-” በማለት የህዳሴን ግድብ ቶሎ ማጠናቀቅ እንደሚገባ ተናግረዋል ።
የብርሀኑ ነጋው ኢዜማም አሜሪካን በግድቡ ውይይት ላይ በታዛቢነት መጥራት ስህተት እንደበረ ገልፆ ጉዳዩን ወደ አፍሪካ ህብረት ወስዶ እልባት ማግኘት እንደሚገባ የጠቆመ ሲሆን የኢትዮጵያን ጥቅም የሚጎዳ ውሳኔ ግን በተአምር ተቀባይነት የለውም ብሏል። የእነ በለጠ አብን ባወጣው መግለጫ “አሜሪካ የኮሎራዶ ወንዝን ተጠቅማ ታላቁን የሁቨር የኤልክትሪክ ሃይል ማመንጫ በ1930ዎቹ መገንባቷ ይታወቃል። ታድያ አሜሪካ ለሜክሲኮ ያልፈቀደችውን ነገር በእኛ ወንዝና ግድብ ለማዘዝ የምትሞክረው በቅኝ ተገዝታ የማታውቀውን ኢትዮጵያን በ neo colonialism እሳቤ ከማስገደድ አይተናነስም።
በእንዲህ አይነቱ ሃገራዊ ጉዳይ ከምንግዜም በላይ ከመንግሥት ጎን እንደሚቆም እያሳወቅን የኢፌድሪ መንግስት በሀገራችን ያሉትን የፖለቲካ ሃይሎችን እና ህዝባችንን በተለያየ ደረጃ ለምክክር እንዲጋብዝ ጥሪአችንን በአክብሮት እናስተላልፋለን።” በማለት ሀገራዊ አንድነቱን አሳይቷል።
የእልደቱ ኤዴፓም ተመሳሳይ መልእክት አስተላልፎ አስፈላጊም ከሆነ ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚያደርግ ገልፇል ። በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት ፍፁም አረጋም ” ኢትዮጵያ በአባይ ውሃ የመጠቀም መብቷን አሳልፎ የሚሰጥ ምንም ዓይነት ስምምነት አትፈጽምም:: ” በማለት የሀገራቸውን አቋም በቲዊተር ገፃቸው አስፍረዋል።
የአሜሪካ ትእዛዝ አናዶት ዛሬ በተከበረው የአድዋ ድል በአል ላይም በሚኒሊክ አደባባይ የወጣው ህዝብ ” ከእኛ በሚነሳው ወንዝ አባይ ግንድ ይዞ ይዞራል ብለን እየዘመርን አኖርም ።እኛም እንደ ግብፅ አስዋንን እንገነባለን ።በድህነት አየኖርን በወንዞቻችን ግድብ ገድበን ኤሌትሪክ እናገኛለን ።ለእርሻችን ውሀ በመስጠት እራሳችንን እንመግባለን ።ከዚህ ማንም አያቆመንም በማለት ።” በሀይማኖት በብሔር ሳይከፋፈል ሲዘምር ታይቷል ።
ጠዋት በተከበረው እና ከዚህ ቀደሙ አንፃር በለጥ ያለ ቁጥር ባስተናገደው ህፃን ፣አዋቂ ፣ወጣትና ሽማግሌ በአማሩ የሀገር ባህል ልብስ የአፄ ሚኒሊክን ምስል በያዙ ቲሸርቶች ታጅባ አዲስ አበባ ለአድዋ ድል ዛሬ ደምቃ ውላ ነበር ።ከሰው ብዛት የተነሳ መኪኖች አስከ ቀን 8 ሰአት ድረሰ ወደ ፒያሳ፣አዲሱ ገበያ፣አራት ኪሎ፣ካሳንችስና መገናኛና እንደ ወትሮ መንቀሳቀስ አልቻሉም ነበር።
በሚኒሊክ አደባባይ የፓሊስ ማርሽ ቡድን የሟቹን የጥላሁን ገሰሰን ዘፈን ” እናት ኢትዮጵያ ” እያለ በከበሮ እና በታራምፔት ሲያሰማ በአብዛኛው የበአሉ ታዳሚ የኮረኮረ የሀገር ፍቅር ካቀረረ እንባ ጋር ፊቱ ላይ ይታይ ነበር ።
አሁን ለጊዜውም ቢሆን የዪንቨርሰረቲ ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታ ያፈናቀለው ብሔር ተኮር ትንኮሳ ፣ በመቶ በሚቆጠር ያስገደለውን የእርስ በእርስ ግጭት ።በብሔር ፍቅር ወድቀው የሚንገጫገጩትን ፓለቲከኞች ሳይቀር የህዳሴ ግድብ የግብፅ በአሜሪካ በኩል ተፅእኖ ለማሳረፍ መሞከር ለጊዜውም ቢሆን ” it is my dam ” ( የእኔ ግድብ ነው) አስብሎ ሀገራዊ ህብረት አሳይቷል።የግብፅ አሜሪካን አደራዳሪ አርጎ ኢትዮጵያን ግድብ እንደሰትሰራ ማድረግ ሁሉንም አስቆጭቶ የውስጥ ንትርኩን ጋብ አድርጓል ።ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያን ወደ አንድንነት መንፈስ በዘላቂነት አድሶ ህብረትን ያመጣል ለማለት ግን ጊዜ የሚፈልግ ይሆናል! !

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *