በዚህ ሳምንት መጀመርያ በመንግስት የፀጥታ ሀይሎች ተይዘው በጉምሩክ ኮሚሽን የአዲስ አበባ ቃሊቲ ጉሙሩክ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት የታሰሩትና በአዲሰ አበባ ፣በኦሮሚያ፣በአማራ እና በደቡብ በ2 ቁጥር ታርጋ መሀል ሸገር ላይ ሲንቀሳቀሱ የነበሩት D4D ፣ዳማስ እና ዶልፊን መኪኖቻቸው በመጪው ማክሰኞ ለባለቤቶቹ እመልሳለው ማለቱን መኪናቸው የታሰረባቸው ባለ ንብረቶች ለፊደል ፓስት ተናግረዋል። ወደ 60 የሚጠጉ መኪኖች የታሰሩ ሲሆን በሺዎች የሚቀጠሩ ተመሳሳይ መኪኖች ከመታሰር ለመዳን ከማድርያቸው በዚህ ሳምንት አልወጡም ።
መኪናቸው ከተወሰደባቸው የተወሰኑት ባለንብረቶች ለፊደል ፓስት በስልክ እንደተናገሩት ዛሬ ጠዋት ቃሊቲ ወደሚገኘው ኮሚሽኑ ፅ/ ቤት እንዳመሩ ገልፀው ማመልከቻ ፅፈው መኪናቸውን መውሰድ እንደሚችሉና በኮድ ሁለት ለመቀጠል የሚፈልጉ ከሆነ የተጣለባቸውን ግብር መክፈል አልያም ታርጋቸውን ኮድ አንድ ወይም ሶስት ማድረግ እንደሚጠብቅባቸው ተነግሮናል ብለዋል።
ኮሚሽኑ የጣለባቸው ግብር ከ 700 ሺ ብር እሰከ አንድ ሚልየን ብር ሲሆን ባለንበቶቹም ይሄ ህገወጥ አሰራር ነው ሲሉ ሰሞኑ ተደምጠዋል።
የኮሚሽኑ ሀላፊዎች ሰሞኑን እንደገለፁት መኪኖቹ በህዝብ አገልግሎት ሰበብ ገብተው በግል አገልግሎት ሲሰሩ በመገኘታቸው ነው ለግል አገልግሎት በሚቀረጥ የቀረጥ ሂሳብ እንዲከፍሉ የተገደዱት ያሉት ብሏል።
የመኪኖቹ ባለቤት ደግሞ “ጉምሩክ ባለስልጣን በህግ መከሰሰ አለበት።። ይህ ህገመንግስታዊ መብታችን ነው። የዜጎችን ንብረት አግባብነት ባሌለው በማስፈራራት መንገድ ነጥቆ ህዝብን ቤተሰብን ለማይገባ እንግልት ከመዳረጉ ባለፈ በወቅቱ ህግን ተላልፎ በሙስናና በሽርክና መኪኖቹ ሀገር ውስጥ ካስገቡ በኋላ በሆጋዊ መንገድ በላቡ የገዛ ባለንብረትን ላልተገባ አገልግሎት አውላችኋል የማለት ስልጣንም ድፍረትም ሆነ የህግ አግባብነት የለውም ” ብለዋል።