የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ጨምሮ በሀገሪቱ ያሉ የግል ባንኮች በተቀማጭነት ያስቀመጡት ገንዘብ ከሰጡት ብድር ጋር ስላልተጣጣመ ለደንበኞቻቸው የሚሰጠው ብድር ካለፈው አንድ ወር ጀምሮ እጅግ መቀነሱን የባንክ ሰራተኞች ለፊደል ፓስት ተናግረዋል።
አብዛኞቹ ባንኮችም ካላቸው ተቀማጭ ገንዘብ ከ70 እሰከ 90 ከመቶ ብድር ላይ በማዋላቸው የገንዘብ እጥረት ገጥሟቸዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለላኪዎች፣ መድሀኒትና ዘይት አቅራቢዎችእንዲሁም ሌሎች ለሀገሪቱ የግድ አስፈላጊ ከሆኑ ምርቶች በስተቀር ለሀገር ውስጥ እቃዎች ግዢም ይሁን ለሌሎች እቃዎች የሚሰጠውን ብድር እንዳቆመ ስማቸው እንዳይገለፅ ያልፈለጉ የባንኩ ሰራተኞች ለፊደል ፓስት ተናግረዋል። ንግድ ባንክ ለሰራተኞቹ የሚሰጠውን ብድር በተቀማጭ ገንዘብ ማነሱ ምክንያት እንዳቆመ ተናግረዋል።
በዳሽን ባንክ የምትሰራ አንዲት ሰራተኛም ብድሮች እንደድሮ እየተለቀቁ እንዳልሆ ተናግራለች ።
እንደሰራተኞቹ ገለፃ ባንኮች የብድር አለቃቀቃቸውን ካላቸው ተቀማጭ ገንዘብ ጋር አመጣጥኖ አለመሄድ፣ የኢኮኖሚው መቀዝቀዝ ፣የዋጋ ንረት ባንኮችን ተቀማጭ ገንዘባቸው እንዲቀንስ አድርጎ የብድር አገልግሎታቸው እንዲቀነስ አድርጎታል ።
ይሄም ችግርን ለመፍታት ኢኮኖሚውን ማቅናትና የሰጡትን ብድር የመመለስ ረጅም ስራ ይጠብቃል በማለት የባንክ ሰራተኞቹ አስተያየታቸውን ገልፀዋል።