በመንግስት የፀጥታ ሀይሎች በመንገድ ላይ እንድንቆም እየተደረገ መኪናቹ በህገወጥ መልኩ በሌላ አገለግሎት ተሰማርቷል ተብለን አስከ 800,000 ብር ደረስ ቀረጥ ተጠይቀናል ያሉ ግለሰቦች ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ በሚገኙበት የከተማው መስተዳደር ደጃፍ ዛሬ ጠዋት በመገኘት ቅሬታቸውን አሰምተዋል። ቅሬታ አሰሚዎቹ ለፊደል ፓስት እንደተናገሩት 600 የሚጠጉ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በአዲሰ አበባ እና በደቡብ ክልል በ2 ቁጥር ታርጋ የተሰጣቸው D4D እና ዳማስ መኪኖቻቸው እንደታሰሩባቸው ገልፀዋል ።
መኪናቸው ከተወሰደባቸው መሀል ሰዒድ ጠሀ እንዲህ በማለት ስለተፈጠረው ድርጊት ያስረዳል ” ከትናንት በስቲያ መሳርያ የያዙ ፓሊሶች መንገድ ላይ አስቆሙኝ ።ምን ተፈጠረ ስላቸው ትፈለጋለክ ብለው ወደ ጉሙሩክ ፅህፈት ቤት ወሰዱኝ ።እዛም መኪናክ ለህዝብ አገልግሎት ወስደክ ለግልክ ስራ በማዋልክ 700, 000 ብር ቀረጥ ክፈል አሉኝ ።በጣም ግራ የገባኝ መኪናዬን በ2 ቁጥር ታርጋ ሳወጣ ፍቃድ የሰጠኝ የመንግስት አካል ነው ።ይሄ ስህተት ከሆነ መጠየቅ ያለበት እራሱ መንግስት እንጂ እኔ አይደለሁም” በማለት ቅሬታውን ገልፇል።
በጉምሩክ ኮሚሽን የአዲስ አበባ ቃሊቲ ጉሙሩክ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት የበተነው ሰርኩርላር ደብዳቤ እንደሚያሳየው መኪኖቹ በህዝብ አገልግሎት ሰበብ ገብተው በግል አገልግሎት ሲሰሩ በመገኘታቸው ነው ለግል አገልግሎት በሚቀረጥ የቀረጥ ሂሳብ እንዲከፍሉ የተገደዱት ያሉት ብሏል።