የእንጀባራው የአቶ ደመቀ መኮንን ሙሉ ንግግር – “እኛም በደምቢዶሎው እገታ ከልባችን አዝነናል”

የተከበራችሁ የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች
የብሄረሰብ አስተዳደሩ ነዋሪዎች
የእንጅባራ እና አከባቢው ነዋሪዎች
ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶች
ክቡራትና ክቡራን

እነሆ! በታሪክ “ፈረስ እና ፈረሰኞች” ለእናት ሃገራቸው ያበረከቱት አስተዋጽኦ በሚዘከሩበት ታላቅ መድረክ ላይ እንኳን በጋራ ለመታደም አበቃን!!
አንጋፋው የሰባት ቤት አገው ፈረሰኞች ማህበር 80ኛ ዓመት የምስረታ በዓል፤
እንኳን በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን!

ሁላችንም እንደምናውቀው. . . የአዊ ብሔረሰብ የበርካታ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ሀብቶች፣ የባህል ዕሴቶች እና ማኅበራዊ ክዋኔዎች ባለቤት ነው። በተለይ በአገው ሕዝብ ታሪክ ዘንድ ፈረስ ልዩ ቦታ ያለው ሲሆን ከዕለት ተዕለት ኑሮ እስከ ዐርበኝነት ተጋድሎ የዘለቀ የታሪክ ከፍታ ይስተዋልበታል፡፡ 
የአገው ፈረሰኞች በዐድዋ ዘመቻ ተሳትፏቸው ለሀገራችን ክብርና ነጻነት ያጎናፀፉ ሲሆን፤ በሁለተኛው የጣልያን ወረራ ጊዜም ዳግም ዘምተው ድል በመቀዳጀት ረገድ ያበረከቱት ድርሻ ትውልድ የሚዘነጋው አይደለም፡፡
የዛሬው መድረክ የጥንቱን ከዛሬና ከነገ የሚያስተሣሥር ታሪካዊ ዕሴት ሲሆን፤ ዛሬ ልንከተለው የምናስበው የብልጽግና መንገድም የዚሁ አብነት መገለጫ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው፡፡ 
በትውልድ እና በዘመን ቅብብሎሽ የደረስንበት ታሪክ የሚሰጠን ፍቺ . . . ከትናንት በጎ ታሪክ ላይ በመነሣት፤ ዛሬ የሚገባንን በመሥራት፣ ለነገ የምትሆን ታላቅ ሀገር መገንባት እንደሚቻል ነው፡፡ 
የአባቶቻቸውን ታሪክና ገድል ያስታወሱት ቀደምት ፈረሰኞች ይህን ማኅበር መስርተው፤ የትናንቱን ድል እያሰቡ ብቻ መቀመጥ ባለመምረጣቸው ከትናንቱ የሚልቅ ድል ለማስመዝገብ እንደሚቻል በተግባር በማረጋገጥ – እኛንም በአንድ ትልቅ ሃሳብ ጥላ ስር እንድንሰለፍ አድርገውናል፡፡
ይህን ታላቅ ኃይል ለሕዝቦች አንድነት፣ ለሀገራዊ ብልጽግናና ለለውጥ መጠቀም የኛ ድርሻ ይሆናል፡፡ 
ሃገራችን ዛሬ እጅግ በጣም በሚያጎመጁ ተስፋዎች እና ይሄን በሚፈታተኑ ተግዳሮቶች ውስጥ ትገኛለች፡፡ በእንዲህ ዓይነት ወቅት የለውጥ ደጋፊዎች እና አደናቃፊዎች የሚጠበቅ ክስተት ቢኖርም፤ ጉዟችን አንድ እርምጃ ወደፊት አንድ እርምጃ ወደ ኋላ ከቶውኑ ሊሆን አይገባም፡፡
በተለይም በያዝነው የለውጥ ጉዞ ጠንካራ ሃገር ገንብተው ለማለፍ በሚተጉ እና ሃገርን አደጋ ላይ ለመጣል ብሎም ለማፍረስ በሚያደገድጉ ሃይሎች መካከል በሚደረግ የትግል አሰላለፍ ላይ በመሆናችን፤ ትውልዱ ዛሬ ከገጠመን ፈተና በዘላቂነት የሚያሻግረውን መንገድ በጥንቃቄ እና በማስተዋል መከተል ይኖርበታል፡፡
ክቡራትና ክቡራን
ይህን ታላቅ በዓል በድምቀት በምናከብርበት ድባብ ጎን ለጎን እንደሃገር ከገጠሙን ፈተናዎች መካከል ከወላጆቻቸው ተነጥለው መንግስትን በማመን በደምቢዶሎ ዩኒቨርስቲ የሚማሩ ተማሪዎች የመታገት ጉዳይ አንዱ ወቅታዊ ፈተና ነው፡፡
ተማሪዎቹ ከታገቱበት ጊዜ ጀምሮ በወቅቱ መፍትሄ አለመሰጠቱ እና ተጨባጭ ውጤት ላይ አለመደረሱ የወሰደው ረጅም ጊዜ የታጋች ተማሪዎች ቤተሰቦች ባልተቋጨ ጭንቀት እና ባልተፈታ ሃዘን ውስጥ ለመክረም መገዳዳቸው የመንግስት ሃላፊነት እና ጉድለት ይሆናል፡፡
ከችግሩ ውስብስብነት አንፃር በተለያዩ ወገኖች ያልተጣሩ እና ተለዋዋጭ መረጃዎች መሰራጨታቸው የታጋች ቤተሰቦችን ስጋት እና ጭንቀት እጅግ መራር እንዳደረገው በገፅ ለገፅ ውይይት ለመረዳዳት የተሞከረ ሲሆን፤ እኛም እንደወላጅ በተፈጠረው አሳዛኝ ክስተት ተሰምቶናል፤ ተፀፅተናል፤ ከልባችን አዝነነናል፡፡
እንደሚታወቀው ቀጠናው የሰላም እና የፀጥታ ችግር የሚስተዋልበት በመሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎችም በተደጋጋሚ የችግሩ ሰለባ ሆነው የቆዩ ሲሆን፤ አሁንም የተማሪዎቹን ጉዳይ በአጭር ጊዜ ውስጥ አንድ የተጨበጠ ውጤት ላይ ለመድረስ፤ ማህበረሰቡን ባሳተፈ መልኩ መንግስት ሙሉ ሃይሉን አሰባስቦ በመረባረብ ላይ ይገኛል፡፡
በዩኒቨርስቲዎቻችን የተረጋጋ ድባብ እንዳይሰፍን ፍላጎት ባላቸው አካላት ከዚህ በከፋ ደረጃ ጉዳት እንዳይደርስ እና አስተማማኝ ሰላም እንዲረጋገጥ በየደረጃው የምንገኝ አካላት በተግባር የመፍትሄ አካል ሆነን መገኘት የሚጠይቀን ታሪካዊ ምዕራፍ ላይ እንገኛለን፡፡

በዴሞክራሲያዊ መንገድ ስሜትን መግለፅና ለዜጎች መብት መከበር መቆም የስልጣኔ ማሳያ ሲሆን፤ በየደረጃው የሚገነኘው የመንግስት አካል ስህተትን ላይደገም በማረም፤ እንዲሁም ተጨባጭ ሁኔታው በታሰበው ልክ ያልፈቀደውን በግልጽ በማሳወቅ ሁሉም የመፍትሄ አካል እንዲሆን ማድረግ ሃላፊነትም ግዴታም ነው፡፡
ከዚህ ውጭ ፅንፈኞች ሃገር ለማፍረስ ዓላማቸው እንዳይጠቀሙበት መጠንቀቅ ይገባል፡፡
ክቡራትና ክቡራን
በአገው የፈረስ ባህል አንድ ፈረሰኛ ፈረሰኛ ለመባል ለፈረሱ፡- ኮርቻ፣ ፋርኒስ፣ ለኮ፣ ወዴላ፣ ምቹና ግላስ ያስፈልገዋል፡፡ ለራሱ ደግሞ፤- አለንጋ፣ ዘንግ፣ ገንባሌ፣ ሳርያን ኮት፣ ጀበርና ሊያሟላ ይገባል። ጦር፣ ጋሻና ሌሎች ካሉት ደግሞ እሰየው ነው። ይህም የሚያሳየን ፈረሰኛ ለእራሱም ለፈረሱም አስቦ ነው የሚኖረው፡፡ ይህ ታላቅ ዕሴት ነው፡፡ 
በኢትዮጵያችን ስንኖርም ለእራሳችንም ለሀገራችን እያሰብን መሆን እንዳለበት የሚስተምረን ነው፡፡ ጥሩ ፈረስ ያለ ጥሩ ፈረሰኛ፤ ጥሩ ፈረሰኛም ያለ ጥሩ ፈረስ ዋጋ የላቸውም፡፡ መልካም ሀገር ይዘን መልካም ዜጋ ከጠፋ፤ መልካም ዜጋ እና መልካም ሃገር ይዘን የሰለጠነ ተጠያቂነት የሰፈነበት የህግ የበላይነት የተረጋገጠበት ስርዓት ይዘንም መልካም ሀገር ከሌለ ዋጋ የለንም፡፡ የምንሠራው ሥራ ለራሳችንም ለሀገራችን የሚጠቅም መሆኑን ምንዜም ማረጋገጥ አለብን፡፡ 
በመጨረሻም በየዓመቱ ኢትዮጵያውያን የቀደሙ አባቶቻቸው ተጋድሎ ለመረዳት፤ የአገው ሕዝብ ደግነትና ፍቅር ለማየት፤ የአዊን ብሄረሰብ አስተዳደር ታሪካዊና ተፈጥሯዊ መስሕቦችን ለመጎብኘት የሚተምበት በዓል እንዲሆን ለማስቻል አስፈላጊውን ድጋፍ እንደማይለያችሁ በኢፌድሪ መንግስት እና በራሴ ስም እየገለፅኩ የተሳካ በዓል እንዲሆን እመኛለሁ፡፡ 
አመሰግናለሁ!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *