ከ2019 ዓ.ም. ጋር ሲነጻጸር በ2020 ዓ.ም. 31 ሚሊዮን ተጨማሪ ሰዎች በኮቪድ- 19 ምክንያት ለከፋ ድህነት ተዳርገዋል ተባለ

የቢል እና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን ኮቪድ-19 በተባበሩት መንግስታት የዘላቂ ልማት ግቦች (United Nations Sustainable Development Goals) አፈጻጸም ላይ ያሳደረውን አሉታዊ ተፅእኖ የሚተነትኑ አዳዲስ መረጃዎችን የያዘ አምስተኛ ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ዛሬ ይፋ አደረገ።
በቢል ጌትስ እና በሜሊንዳ አን ፍሬንች ጌትስ በጋራ የተረቀቀው የዚህ ዓመት ሪፖርት ኮቪድ-19 ያስከተላቸው ኢኮኖሚያዊ ልዩነቶች አሁንም እየሰፉ መሆኑንና በወረርሽኙ በጣም የተጎዱት ሃገራት ለማገገምም ተጨማሪ ጊዜ እንደሚወስድባቸው ያሳያል፡፡ ከ2019 ዓ.ም. ጋር ሲነጻጸር በ2020 ዓ.ም. ብቻ 31 ሚሊዮን ተጨማሪ ሰዎች በኮቪድ- 19 ምክንያት ለከፋ ድህነት ተዳርገዋል። 90% የሚሆኑት ያደጉ ሃገራት በሚቀጥለው ዓመት ከወረርሽኙ መከሰት በፊት ወደነበሩበት የነፍስ ወከፍ ገቢ ደረጃ ይመለሳሉ፣ ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሃገራትም ይህን እንዲያደርጉ ጥረቶች እየተደረጉ ነው።
ይሁንና ሪፖርቱ በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም እንኳን ከዚህም የከፉ ሁኔታዎችን ለማስቀረት ዓለም በጋራ መቆሟን በበጎነት አንስቷል። ያለፈው ዓመት ተመሳሳይ ሪፖርት፣ የጤና ሜትሪክስ እና ግምገማ ኢንስቲትዩትን (IHME) ጠቅሶ የዓለም አቀፍ የክትባት ሽፋን የ14 በመቶ እንደሚቀንስ ተንብዮ ነበር፤ ይሁንና የተቋሙ አዲስ ትንበያ እንደሚያሳየው፣ አሁንም ተቀባይነት ባይኖረውም፣ ውጤቱ ከተጠበቀው በግማሽ ያህል ሊያሽቆለቁል ይችላል።
በሪፖርቱ ውስጥ ሊቀመናብርቱ ቢልና ሜሊንዳ “አስደናቂ ፈጠራዎች” በሚል ያሞካሹትን አሠራር ለማሳካት ዓለም ዓቀፍ ትብብር፣ ቁርጠኝነት እና ቀጣይነት ያለው ኢንቨስትመንት ቢያንስ ለቀጣዮቹ አስር ዓመታት ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው። እንደሪፖርቱ ገለጻ የከፋ ሁኔታዎችን ለማስቀረት የተደረጉ ጥረቶች በሙሉ የሚያስመሰግኑ ናቸው፤ ይሁንና ብቻቸውን ግን በቂ አይደሉም። በወረርሽኙ ከተጎዳው ኢኮኖሚ በአስተማማኝ ሁኔታ ለማገገም፣ የመልሶ ማቋቋም ጥረቶችን ለማፋጠን እና ዓለምን ወደ ትክክለኛው ጎዳና ለመመለስ፤ ፈጣን የኮቪድ -19 ክትባትን ለማበልጸግ የተደረጉ ጥረቶችን የመሳሰሉ በኢኮኖሚና በጤና ዘርፍ የሚደረጉ የረዥም ጊዜ ኢንቨስትመንቶችን አስፈላጊ ናቸው ሲሉ ሊቀመናብርቱ ጥሪ አድርገዋል፡፡
ሊቀመናብርቱ አክለውም “ያለፈው ዓመት አስተማማኝ ዕድገት የሚቻል ግን ደግሞ አድካሚ ነው የሚለውን ዕምነታችንን አጠናክሮልናል” ብለዋል፡፡ “በባለፉት 18 ወራት ያመጣነውን ውጤት ማጠናከር ከቻልን ወረርሽኙን ታሪክ በማድረግ ጤና፣ ረሃብን መከላከልና እና የአየር ንብረት ለውጥ የመሳሰሉ መሠረታዊ ጉዳዮቻችን ላይ በማተኮር የተቀዛቀዘውን ዕድገት በድጋሚ እንዲያንሰራራ ማድረግ እንችላለን።”
ሪፖርቱ በሌላ በኩል ወረርሽኙ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በሴቶች ላይ ያደረሰውን ኢፍትሃዊ ኢኮኖሚያዊ ተፅእኖ በትኩረት ቃኝቷል። ከፍተኛም ሆነ ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው አገራት በተመሳሳይ ወረርሽኙ ባስከተለው ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ቀውስ ሴቶች ከወንዶች በባሰ ሁኔታ ተጎጂ ሆነዋል።
ሜሊንዳ አን ፍሬንች ጌትስ በበኩላቸው “በአራቱም የዓለም ማዕዘናት ሴቶች በርካታ መዋቅራዊ መሰናክሎችን ይጋፈጣሉ፣ ይህም በወረርሽኙ ወቅት ሴቶችን ይበልጥ ተጠቂ አድርጓቸዋል” ብለዋል። መንግስታት በሴቶች ላይ ይበልጥ ኢንቨስት በማድረግ እና መሰል ኢ-ፍትሃዊነቶችን በማስወገድ ሴቶች ኢኮኖሚያቸውን በማጠናከር በፍጥነት እንዲያገግሙና ወደፊት ከሚመጣ ቀውስ ራሳቸውን እንዲከላከሉ ሊረዷቸው ይገባል ብለዋል፡፡ ይህን ማድረግ ትክክለኛው ነገር ብቻ ሳይሆን – ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ አስተማማኝ የፖሊሲ አማራጭ ነው።
ሪፖርቱ በተጨማሪም “ተዓምር” የተባሉት የኮቪድ -19 ክትባቶች ሥርጭት ፍጥነት ለአስርት ዓመታት በመሠረተ ልማት፣ በሰው ኃይልና ሥነ ምህዳር ግንባታ የተደከመባቸው የኢንቨስትመንት፣ የፖሊሲና የአጋርነት ሥራዎች ውጤት እንደሆነ አሳይቷል። ይሁን እንጂ እነዚህን ክትባቶች የማበልጸጊያና የማሰራጫው ስርዓት በዋነኝነት በሀብታም ሀገሮች ውስጥ ብቻ ይገኛል ስለዚህም ዓለም በፍትሃዊነት ተጠቃሚ ልትሆን አልቻለችም፣ብሏል፡፡
ቢል ጌትስ በበኩላቸው “የኮቪድ-19 ክትባቶች በፍትሃዊነት ተደራሽ አለመሆናቸው በጣም አሳዛኝ የህዝብ ጤና ጉዳይ ነው” ብለዋል። “ሀብታም ሃገራትና ህዝቦች የኮቪድ-19ን ወረርሽኝ እንደ ሌሎች የድህነት በሽታዎች ማከም የሚጀምሩበትን እውነተኛ አደጋ ወደፊት ይጠብቃቸዋል ስለዚህም የትም ይኑር የት ሁሉም ሰው ክትባት እስካላገኘ ድረስ ወረርሽኙን ታሪክ ማድረግ አንችልም።
እስካ ዛሬ ከ80 በመቶ በላይ የኮቪድ -19 ክትባቶች ከፍተኛና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገሮች ውስጥ ብቻ ሲሰጥ የቆየ ሲሆን አንዳንድ ሃገራት ከሚያስፈልጋቸው ቁጥር በላይ ሁለት እስከ ሦስት እጥፍ መጠባበቂያ ሲይዙ እንደነበር ታይቷል። ባንጻሩ ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ሃገራት ውስጥ የተከፋፈለው ከ1 በመቶ በታች የመድኃኒት መጠን ብቻ ነው። በተጨማሪም የኮቪድ-19 ክትባት ተደራሽነት የክትባት ምርምርና ማበልጻጊያ ማዕከላትና የማምረት አቅም ካሉባቸው ቦታዎች ጋር በጥብቅ መቆራኘቱን ማየት ተችሏል፤ ምንም እንኳን 17 በመቶ የሚሆነው የዓለማችን ህዝብ የሚኖረው በአፍሪካ ቢሆንም ክትባት የማምረት አቅሟ ግን ከ1 በመቶ በታች ነው።
በመጨረሻም፣ ሪፖርቱ ዓለም የምርምር ማበልጻጊያ ማዕከላትን ለመገንባት፣ መሠረተ ልማትን ለማስፋፋት እና ለፈጠራ የሚያደርጋቸውን ኢንቨስትመንቶች ተጠቃሚው የሰው ልጅ ወደሚኖርባቸው ሥፍራዎች እንዲያደርግ ጠይቋል፡፡
ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው አገሮች የሚገኙ ተመራማሪዎችን እና አምራቾችን አቅም ለማሳደግና ለመገንባት የሚያስፈልጋቸውን ክትባትና መድኃኒት ማበልጸግ እንዲችሉ ለማድረግ በሃገራቱ ውስጥ የሚገኙ አጋሮች ላይ መዋዕለ ንዋያ ማፍሰስ ያስፈልጋል ሲሉ የጌትስ ፋውንዴሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ ማርክ ሱዝማን ተናግረዋል።
ታላላቅ የጤና ተግዳሮቶቻችንን የምንፈታበት ብቸኛው መንገድ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሰዎችን ፈጠራና ክህሎት በመደገፍ ብቻ በማለት ማርክ ሱዝማን መፍትሄ ያሉትን ሐሳብ ተናግረዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *