በተስፋዬ ጌትነት
ታዛቢ ተብላ ከአለም ባንክ ጋር የተጋበዘችው አሜሪካ 300 ሚልየን ዶላር እንዳለው በሚገመተው የግምጃ ቤት ሀላፊዋ ሀብታሙ ስቴቨን ሙኒችን በኩል ባወጣቸው መግለጫዋ ፈላጭ ቋራጭ ሆና ግብፅና ሱዳን ካልተስማሙ በስተቀር ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ውሀ መሙላት ወይንም ሀይል ለማመንጨት ሙከራ ማድረግ እንደማትችል አሳውቃለች ። በአሜሪካ መግለጫ የተበሳጨውም በድህነት የሚኖረው የኢትዮጰያ ህዝብም ለምን? ሲል የፕሬዝዳንት ትረምፕ አስተዳደር ላይ ተቃውሞውን በማህበራዊ ድህረ ገፅ ” የኔ ግድብ ” ( it’s my dam ) በማለት ሲገልፅ ተስተውሏል ። ሰባ ከመቶ የገጠር ህዝቧ መብራት በማያገኝበት 110 ሚልየን ህዝብ ከ4,200 ሜጋ ዋት ያልበለጠ የኤሌትሪክ ሀይል ሲያመነጭ ሊያውም ከራሱ ወንዝ በሚነሳ ወንዝ ግድብ ሲሰራ” ቆይ እኔ አውቅልሀለው ሲባል ” ቁጣውን ቢገልፅ አያስገረምም።
ግብፅ ኢትዮጵያን እንዴት ሸወደች?
አቶ መለስ ዜናዊ ከሰባት አመት በላይ ፕሮጀክት “X” ብለው በሚስጥር ደብቀው ቀን እየቆጠሩ የያዙትን ነገር የግብፅ ፕሬዝዳንት ሆስኒ ሙባረክ ከስልጣን ይውረዱ ተብሎ ተቃውሞ ሲነሳ መጋቢት 24 ,2003 ዓ.ም “የታላቁ ህዳሴን ግድብ” በማለት ይፋ አደረጉት። ።ለአመታት ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ግድብ እንዳትገነባ ሲሰልሉ ብድርም ለእንደዚህ አይነት ስራ እንዳታገኝ አለም ባንክን ጨምሮ ሌሎች አለም አቀፍ ተቋማትን በማሳመን የተሳካላቸው ግብፅ ፓለቲከኞች አቶ መለስ በአባይ ወንዝ ላይ በቤንሻንጉል ጉባ በተባለ ስፍራ ላይ የነደፉትን ፕሮጀክት አንደማንኛውም ሰው ነበር በቴሌቭዝን የተመለከቱት ። አቶ መለስ አባይ ላይ ተንተርሶ ለግድብ ብር ስጡኝ ቢሏቸው ለዘመናት እንቢ ያሉትን እነ አለም ባንክን ” ግድቡ የሚገነባው በእኛ በኢትዮጵያውያንና በመንግስት ነው ” እንዲሁም “መሀንዲሶቹም እኛው” በማለት አለም ባንክን ግድቡ ላይ እንደማይፈልግ ተናግረዋል ።የግብፅ ጋዜጠኛም አዲስ አበባ መጥቶ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር 1959 በግብፅና በሱዳን የተፈረመውን ከወንዙ ውሀ ላይ ግብፅ 55.5 ቢልየን ኪዮቢክ ሜትር ሱዳን 18.5 ቢልየን ኪዮቢክ ሜትር ውሀ በአመት እንዲወስዱ የአባይን ወንዝ አጠቃቀም የተፈረመውን ውሳኔ ኢትዮጵያ እየተጋፋች ነው ብሎ ላቀረበላቸው ጥያቄ ” ኢትዮጵያ ባልፈረመችበት ውሳኔ የመተዳደር ግዴታ የለባትም ። አሁን እኔ ብቻ ልጠቀምበት የሚባልበት ዘመን አይደለም! ” በማለት መልሰው እንደነበር ይታወሳል ።ግብፆችም እንደራደር ብለው ሲመጡ” የለም ወንዙን የሚነካቸው11 ሀገሮች እንጂ በኢትዮጵያ፣ግብፅና ሱዳን አይወሰንም “ብለው በመከራከር ታንዛኒያን ፣ኡጋንዳን ፣ሩዋንዳን ፣ደቡብ ሱዳንን ቀልብ መሳብ ችለው ነበር ።
ግድቡ ህዝባዊ ስሜት እንዲኖረው የቦንድ ግዢ እንዲደረግ ያስጀመሩት ስራ መልካም ነበር ። ነገር ግን የህዳሴን ግድብ አሌክትሮ መካኒካል ክፍሉን ወታደራዊው ሜቴክ ይስራ ብለው ሲወስኑ በቂ ጥናት አለማድረጋቸው ሜቴክ ስራው ላይ ያበላሻቸውና ስራዎች ያቃጠላቸው ግዚያቶች ምስክር ናቸው ። የግድቡን የምህንድስና ክፍል የያዘው የጣልያኑ ሳሊኒ ካምፓኒ ሜቴክ ባዘገያቸው ስራዎች ስራ መስራት እንዳልቻለ ለዚህም ካሳ እንዲከፈለው መጠየቁ ሜቴክ ግድቡ ስራ ላይ የነበረውን ድክመት እንድንፈትሽ ያደርገናል። መጋቢት 24 ,2003 የተጀመረው ስራ ሀምሌ 7,2009 መጠናቀቅ ነበረበት ። ደካማ የመንግስት ፕሮጀክት አፈፃፀም ግድቡን ከተያዘለት አምስት አመት አይደለም በዘጠኝ አመት እንዲጠናቀቅ አላደረገውም ።ይሄ ደግሞ የግድቡን ግንባታ የምታቀወመውን ግብፅን ትንፋሽ አግኝታ አሜሪካንን ሸምግይ ብላ ጠርታ ተፅኖ እንድታሳድር አድርጓታል።
ግብፅ የአቶ መለስ መሞትን ተከትሎ ስልጣን የያዙትን አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን ካርቱም ከአምስት አመት በፊት ” ኑ ” ብላ “የግድቡ ጉዳይ ሳይቋጭ ቢቀር አደራዳሪ እንጥራ “ብላ ነገር ሰትጠነስስ አቶ ኃይለማርያም በወቅቱ የሱዳኑ መሪን አልበሽርን የግብፁን ፕሬዝዳንት አል ሲሲን ይዘው ተጨባብጠው ዛሬ እዳ የሆነብንን ሰነድ ፈርመዋል ።የተደገሰውን ድግስ ቀድመው አልተረዱም ነበር ። የግድቡ ቦርድ አመራር የነበሩት የአሁኑ የትግራይ ም/ል ርዕሰ መሰተዳደር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ተው ይሄ ነገር ጣጣ ያመጣል ብሎ አቶ ኃይለማርያምን መምከር ሲችል ግብፅ እኛን ወደ ምትጎዳበት ሜዳ ስትከተን ድምፅ አላሰማም ነበር። ደብረፅዮን ከሶስት አመት በፊት በሰጡት መግለጫ 60 ፐርሰንት ተጠናቋል ሀይል ማመመንጨት ሊጀመር ነው ቢሉም በተጨባጭ አሰከ አሁን የታየ ነገር የለም።በካርቱሙ ስምምነት ላይ በወቅቱ የውሀና ኢነርጂ ሚኒስትር የነበሩት አቶ አለማየው ተገኑ ” አደራዳሪ ” የሚለውን አንቀፅ ምሁራንን ሰብስበው ሳያስረዱ ኃይለማርያም ሲፈርም እንደ ሰርግ ጋብቻ “ኢትዮጵያ አለምሽ ዛሬ ነው ” ብለው አጭብጭበዋል። ምክትል ጠ/ሚኒስተር ደመቆ መኮንንም እንደ ግድቡ የህዝባዊ ተሳትፎ ቦርድ አባልነታቸው የካርቱሙን ስምምነት ከመፈረሙ በፊት ቆይ እንምክርበት ማለት ሲገባቸው ያሰሙት ነገር የለም።በወቅቱ የካርቱሙን ስምምነት አስቀድመው የተቃወሙትና ጠንከር ያለ ተቃውሞ ያሰሙት የአሁኑ በኩባ የኢትዮጵያ አምባሳደር የ60 አመቱ ሰዉዬ አቶ አስፋው ዲንጋሞ ነበሩ።የሚሰማቸው ሰው ግን አልነበረም።
ግብፅ እስራኤልን እንደሀገር ቆጥራ የተቀበለች የመጀመርያዋ አረብ ሀገር እንደመሆና መጠን አሜሪካ በአመት አስከ ሁለት ቢልየን ዶላር ድጋፍ የምታረግላት ሀገር ናት ። በግብፅ በሰው ሰራሹ ሲውዝ ቦይ 9% የአለም የንግድ እንቀስቃሴ በመርከብ ይተላለፍበታል። ።በዚህም በአመት እስከ ግማሽ ቢልየን ዶላር ታገኛለች ።ሲውዝ ቦይ ስራ ቢያቆም አለም አቀፍ የንግድ ቀውስ ይመጣል ።የሸቀጦችም ዋጋ ይንራል።የግብፅ አስራኤልን ጀርባ ብትሰጥ በአረቦች የማትወደደው እስራኤል ጥቃት ሊደርስባት ይችላል።ስለዚህ ግብፅን መደገፍ ለእስራኤል የህልውና ጉዳይ ነው ።የእስራኤል ቀኝ እጅ አሜሪካም እስራኤል እንዳትነካ እንዲሁም ከመካከለኛው ምስራቅ የሚነሳ የአሜሪካ ጠላትን መቆጣጠር የምትችለው ግብፅ ጋር ተባብራ ስለምትሰራ ነው ።በዚህ ነገሯ አሜሪካን የያዘችው ግብፅ አሜሪካን ታዛቢ አርጋ ከዛም በማይታወቅ ሁኔታ አሜሪካ ወደ አደራዳሪ አድርጋ 6,000 ሜጋ ዋት ያመነጫል 78 ቢልየን ኪዮቢክ ሜትር ውሀ ማቆር ይችላል የተባለውን በአፍሪካ አንደኛውን በአለም ስምንተኛውን የኤሌትሪክ ግድብ ስራ ግቡን እንዳይመታ ላይ እታች እያለች ትገኛለች ።
በግድቡ ላይ የአልበሽር ሱዳን ለኢትዮጰያ መወገኑ ያስቆጣት ግብፅ አልበሽር ከስልጣን ወርዶ እስር ቤት ሲወረወር የአሁኑ የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትርን አብደላ ሀምዱክን አሳምና ከጎኗ ማሰለፍ ችላለች።ሀምዱክ ሱዳን ለዘመናት እንደ ሀገር አይታ የማታያትን እስራኤል ጋር ወዳጅነት በመፍጠር ከአስራኤል ጠ/ሚ ኔታንያሁ ጋር ኡጋንዳ ካምፓላ በመገናኘት ወዳጅነት ለመመስረት ጥረዋል።
ሀምዱከ በቀጣይ ከአሜሪካ ጋር በመወዳጀት በሀገራቸው የተጣለውን ማእቀብ ለማስነሳት ይሰራሉ ተብሎ ይጠበቃል ።ለእዚም ከጎረቤት ግብፅ ጋር ያላቸውን ግንኙነት እያጠናከሩ ይገኛሉ ።ግብፅም ይሄን ተጠቅማ በህዳሴ ግድብ ላይ ሱዳን ግብፅን የሚቃረን ሀሳብ ላይ ድጋፍ እንዳታደርግ ግፊት እያረገች ሀሳብም እያስቀየረች ኢትዮጵያን ብቻዋን እንድትቆም እያረገች ነው ።
ግብፅ በድርድሩ ላይ ባቀረበችው ሀሳብ መሰረት የአባይ ወንዝ ከሚያፈሰው አመታዊ 49 ቢልየን ኪዩቢክ ሜትር ውሀ ውስጥ ኢትዮጵያ ግድቡን ለመሙላት መጠቀም የምትችለው ዘጠኝ ቢልየን ኪዮቢክ ሜትሩን ነው እሱንም በክረምት ወቅት ብቻ በማለት ግድቡን ለመሙላት 21 አመት የሚፈጅበትን ሁኔታ በድርድር ላይ አቀርባለች ። ታዛቢዋ አሜሪካም 37 ቢልየን ኪዩቢክ ሜትር ይሁን ብላ ሸምግልና ሀሳብ አቀርባለች ።የአሜሪካም ሆነ የግብፅ ሀሳብ ያልተዋጠላት ኢትዮጵያ 30 ቢልየን ሜትር ኪዩቢክ ሆና ሀሳብ አቅርባለች ። ግብፅ ኢትዮጵያ በድርድሩ ባትስማማ አሜሪካን ከኢትዮጵያ አጣልታ ኢትዮጵያ ማእቀብ እንዲጣልባትና የኢኮኖሚና ጫና የፓለቲካ አለመረጋጋት ኢትዩጵያን እንዲያዳክማት በማድረግ ግድቡን ለማዘግየት ” የአባይ ጉዳይ ለግብፅ የሞት ወይም የሽረት ጉዳይ ነው ” እንዳለችው የተቻላትን ታረጋለች።
የጠ/ሚ አብይ ስህተትና ጥናካሬ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምንም አንኳን ካርቱም ላይ “የአደራዳሪ ” አንቀፁ በእሳቸው ግዜ ባይፈረምም አሜሪካና አለም ባንክን በአደራዳሪነት መጋበዝ አልነበረባቸውም። አሜሪካ ከግብፅ ጋር ያላት ስትራቴጂክ ትብብርነት ከኢትዮጵያ እንደሚበልጥ አሜሪካ ወደ ግብፅ ምታጎርፈውን ዶላር አንብቦ ለመገንዘብ ግዜ አይፈጅም ። አለም ባንክ ሶስት ቢልየን ዶለር ለሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ስራ እሰጣለው ሲል” ነፃ ምሳ” እንደሌለ ሊያመጣባቸው የሚችለውንም ጣጣ እንደ ፓለቲከኛ እንደ ሀገር መሪም መገመት ነበረባቸው ። አደራዳሪም ከተፈገለም የአፍሪካ ህብረትን ወይንም የላይኛው ተፋሰስ ሀገራትን ማምጣት ነበረባቸው ።አሁንም አልረፈደም ።”ደቡብ አፍሪካ ታደራድረን” እንዳሉት በቀኝ ግዛት ስምምነት ከግብፅ ጋር ልንስማማ እንችልም ብለው አፍሪካን ፣አውሮፓን እና አሜሪካን ማሳመን አለባቸው ።ግብፅ ለእስራኤል ህልውና መሰረት እንደሆነች ኢትዮጵያም አልሻባብን በመዋጋት የምስራቅ አፍሪካ ሰላም እንዳስከበረች፣ ከሱማሌም ለቃ ብትወጣ ቀጠናው የአሸባሪዎች መፈንጫ አንደሚሆንና በህንድ ወቅያኖስ በኩል የሚደረገው የመርከቦች እንቅስቃሴ ሊረበሽ እንደሚችል ማስረዳትና ማሳመን ይጠበቅባቸዋል። የግብፅ ህዳሴን ግድብ ማጨናገፍ ሁለቱን ሀገሮች ከማጣላት አልፎ የመካከለኛው ምስራቅን ሰላምን እንደሚያናጋ ይሄም አለም አቀፋዊ ቀውስ እንደሚያስከትል በውጭ ጉደይ ሚኒስትር በኩል ጠንካራ ስራ ሊሰሩ ይገባቸዋል ።
ጠ/ ሚኒስትሩ አሁን እንዳረጉት ግድቡን ክርክሮች ቢኖሩም ግንባታውን በማስቀጠል በመጪው አንድ አመት እሳቸው ወይም በቀጣይ ነሀሴ ምርጫ የሚያሸንፈው ፓርቲ ቢያንስ 700 ሜጋ ዋት በማመንጨት በአመት አንድ ቢልየን ዶላር እንዲያገኝ በማድረግ” ህዳሴ ግድብ መቼም ሀይል አያመነጭም” የሚለውን ጥርጣሬ ማጥራት ያስፈልጋል።
ከምንም በላይ ሶስት አመት በፊት መጠናቀቅ የነበረበትን ግድብ ጨርሶ በቀጣዩ አምስት አመት ዉሀ ሞልቶ ግድቡ ለታለመበት አላማ ማዋል ይገባል።ብዙ በዘገየ ቁጥር ለግብፅ ስኬትን ለኢትዮጰያ ኪሳራና ችግርን የሚወልደው ። ሆኖም ግን አባይ ብቸኛው አማራጫችን ሳይሆን ሎሎቹን የዉሀ፣የንፋስ፣የፀሀይ የሀይል አማራጮች ላይ ስራ መሰራት አለበት ።