አለም አቀፍ የህግ ባለሙያው አቶ እምሩ ታምራት የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚቴ አባል ሆነው ተመረጡ



አስራ ስምንት አባል በሚይዘው በ173 ሀገራት ዙርያ የሰብዓዊ እና ፖለቲካዊ መብቶች ላይ በሚሰራው የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ኮሜቴ ውስጥ የ58ቱ አመት ኢትዮጵያዊ አለም አቀፍ የህግ ባለሙያው አቶ እምሩ ታምራት አባል ሆነው መመረጣቸው ለፊደል ፖስት በስልክ አረጋግጠዋል።

የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ኮሜቴ ላይ እንዲሰሩ በመመረጥ የመጀመሪያ ኢትዮጵያዊ ሲሆኑ ከ20 አመት በላይ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ፣የመሬት አስተዳደርና መብት ፣በአለም ዓቀፍ ንግድ ጉዳዮች ላይ አማካሪ ሆነው በመስራት የካበተ ልመድ እንዳለቸው የግል ማህደራቸው ያሳያል።

እንዲሁም ውሃ ፖለቲካ እና መብት ላይ በአዲስ አበባ ዪንቨርስቲ በአስተማሪነት የሰሩ ሲሆን በናይል ተፋሰስ እና በአካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ላይም ኢትዮጵያን በመወከል ተደራዳሪ ሆነው አገልግለዋል።

የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ኮውንስል አማካሪ በመሆን ለስድስት አመት ያገለገሉ ሲሆን አሁን ለተመረጡበት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚቴ አባልነት ከኢትዮጵያ መንግስት እና ከአፍሪካ ህብረት በኩል ድጋፍ ማግኘታቸውም ተሰምቷል ።

አቶ እምሩ ለመጪው አራት ሀገራት ያለውን የሰብአዊ ፣ፖለቲካዊ እንዲሁም ግለሰበዊ መብቶችን ከመንግስት ፣ከሰብአዊ መብት ተሟጓቾች እንዲሁም ከተለያዩ ማህበራትና ድርጅቶች ሪፖርቶችን በሚገመግመውና በሶሰት ወር አንዴ በኒዮርክ እና ጄኔቫ በሚካሄድ ስብሰባ ላይ የሚሳተፉ ሲሆን መንግስታት ማሻሻል እና ማጠንከር ባለባቸው ጉዳዮች ላይ እንደሚሰሩ ታውቋል ።

” በኢትዮጵያም ይሁን በሌላ ሀገር መሻሻል ያለባቸው የሰብአዓዊና የፖለቲካዊ መብት ጉዳዮች አሉ ።እነሱ እንዲሻሻሉ የአቅሜን አሰራለው ” በማለት አቶ እምሩ ለፊደል ፖስት አስተያየታቸውን ገልፀዋል።

ከአቶ እምሩ በተጨማሪ የግብፅ ፣የሞሮኮ እና የቶጎ ሶስት ምሁራን በኮሚቴው አባልነት እንዲሰሩ ከአፍሪካ ተመርጠዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *