ሳቶ 30,000 የእጅ መታጠቢያ መሳሪያ ድጋፍ ለዩኒሴፍ አደረገ

ሊክሲል በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ14ተኛ በአገራችን 13ተኛ ግዜ የተከበረውን ዓለም አቀፍ የእጅ መታጠብ ቀን ምክንያት በማድረግ ትናንት ጥቅምት 4 /2015 30 ሺሕ ሳቶ ታፕ የእጅ መታጠቢያ መሳሪያዎችን ለዩኒሴፍ ኢትዮጵያ አስረክቧል።

በ44 አገሮች ውስጥ የሚገኝ እና መሰረታዊ የንፅህና አጠባበቅ መፍትሄዎችን ለማቅረብ በኢትዮጵያ ውስጥ በመስራት ላይ የሚገኘው ሊክሲል 70 ሺሕ የአሜሪካን ዶላር ዋጋ ያላቸው የእጅ መታጠቢያ መሳሪያዎችን ነው ለዩኒሴፍ ኢትዮጵያ ያስረከበው።

በርክክብ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የሊክሲል ኢትዮጵያ ሥራ አስፈጻሚ እየሩሳሌም ታዬ ባደረጉት ንግግር፤ “ዩኒሴፍ በዓለም ዙሪያ ያሉ ሕዝቦችን ሕይወት ለማሻሻል የሚያደርገውን ጥረት ለማገዝ በመቻላችን ታላቅ ደስታ ይሰማናል” ያሉ ሲሆን፤ ዘንድሮም ዩኒሴፍ የኢትዮጵያን የንጽህና እና የእጅ መታጠብ ችግር ለመቅረፍ የሚሰራውን ሥራ ለማገዝ ድጋፉን አበርክተናል ብለዋል።

በዩኒሴፍ ኢትዮጵያ የወሽ ዋና ሃላፊ ኪትካ ጎዮል በበኩላቸው፤ ዩኒሴፍ በዓለም ዙሪያ የህዝቦችን ኑሮ ለማሻሻል ተጨባጭ ሥራዎችን በመስራት ላይ እንደሚገኝ ገልጸው፤ ነገር ግን ይህ ጥረቱ ውጤታማ የሚሆነው እንደ ሊክሲል ባሉ ድርጅቶች በሚደረግ ድጋፍ መሆኑን ተናግረዋል። ለሊክሲል ድጋፍ ምስጋናን በማቅረብም ወደፊትም ተመሳሳይ ርዳታ እንደሚደረግላቸው ያላቸውን ተስፋ  ገልጸዋል።

በተጨማሪም በዕለቱ ሊክሲል በአዲስ አበባ ልዕልት ዘነበወርቅ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ያስገነባቸውን መጸዳጃ ቤቶችና የእጅ መታጠቢያዎችን አጠናቆ ለትምህርት ቤቱ አስረክቧል፡፡

ሳቶ ታፕ በአብዛኛዎቹ በአገር ውስጥ ከሚገኙ የፕላስቲክ ጠርሙሶች ጋር ተገጠሞ አገልግሎት መስጠት የሚችል መሳሪያ ሲሆን፤ እጅን በ100 ሚሊ ሊትር ያህል ውሃ በበቂ መታጠብ የሚያስችል ውሃ ቆጣቢ መሳሪያ መሆኑም ተነግሯል፡፡

እ.ኤ.አ በ 2018 ዩኒሴፍ እና ሊክሲል የተሻለ የንፅህና አጠባበቅን ለማስተዋወቅ የሜክ ስፕላሽ መርሃ ግብር መስረተው በጋራ በመስራት ላይ ይገኛሉ።

ዓለም አቀፍ የእጅ መታጠብ ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ14ተኛ በአገራችን 13ተኛ ግዜ “የእጅን ንጽህናን ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ በአንድነት እንስራ!” Unite for Universal Hand Hygiene! በሚል መሪ ቃል ትናንት ጥቅምት 4/2015 በመላው ዓለም ተከብሯል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *