በኢትዮጵያ ፕሬስ ደርጅት ዛሬ መጋቢት 1,2012 ቀትር 5: 50 ገደማ ” ምርጫ ቦርድ የምርጫ ክልሎች ካርታ ይፋ ማድረጊያ ቀንን “አስመልክቶ በድርጅቱ ማህበራዊ ድህረ ገፅ የተለቀቀው ዜና ስር በፎቶ ሾፕ የተቀነባበረው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከባለቤታቸው ቀዳማዊ እመቤት ዝናሽ ታያቸው ጋር መኝታ ቤት ተነጣጥለው የሚያሳየውን ፎቶ በስህተት አንደሆነ እና ጥፋትም እንደሆነ ምስሉን የተጠቀመው ጋዜጠኛ ድልነሳው ምንውይለት የተናገረ ሲሆን ይቅርታም እንደጠየቀ የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ጌትነት ታደሰ ለፊደል ፖስት ተናግረዋል
” ነገሩ እንደተከሰተ ወዲያው ነው ይቅርታ የጠየቀው ።አጥፍቻለው ።የሰራሁት ነገር ስህተት ነው ።” በማለት ጋዜጠኛው ለድርጅቱ እንደተናገረ አቶ ጌትነት ተናግረዋል።
የተቀነባበረው ፎቶ እንዴት ጋዜጠኛው ኮምፒውተር ላይ ሊገኝ ቻለ ?ተብለው የተጠየቁት አቶ ጌትነት ” ልጁ ስህተቱን አምኖ ይቅርታ ጠይቋል ። እኛም እንደ አስተዳደር ከስራ አግደነዋል። ሌላውን ጉዳይ ፓሊስ እያጣራ ስለሆነ ከዚህ በላይ ምንም ልል አልችልም ” ብለዋል።
ፊደል ፓስት ባገኘው መረጃ ጋዜጠኛውን ጨምሮ ሌላ የድርጅቱ የድህረገፅ ክፍል ሀላፊ ከሰአት ፓሊስ ጣቢያ ለምርመራ አቅንተው እነደነበር ታውቋል።