ጤና ሚኒስትር ሊያ ታደሰ የኮሮናቫይረስ በተመለከተ ያወጧቸው ሪፓርቶች 31 ላይ ደርሰዋል ። አስከዛሬ ሚያዝያ 6,2012 ድረስም ኢትዮጵያ ውስጥ 82 ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል ብለውናል ።ከ82 ተጓዦች ደግሞ 30ው ከዱባይ የመጡ ኢትዮጵያውያን ናቸው ።አብዛኞቹ ደግሞ ነጋዴዎች ሲሆኑ የተወሰነ እቃ ከዱባይ አምጥተው የተወሰነ ብር አትርፈው በመሸጥ የሚታትሩ ዜጎች ናቸው።
እነዚህ ዜጎቻችን ዱባይ ሲሄዱ ማደርያም እርካሽ ልብስም እርካሽ የሚያገኙባት ናይፍ አደባባይ አካባቢ በሚገኙ ሱቆች ነው።
ቀድሞ ግመል የሚተራመስበትና የሚጓዝባት ናይፍ አሁን ቅልጥ ያለ የንግድ መንደር ሆኗል ።ከ260 በላይ ሱቆች ያሉት ናይፋ መንደር ከቻይና፣ከህንድ ከአውሮፖና ከአሜሪካ የመጡ ጌጣ ጌጦች፣ ልብሶች ፣ጫማዎች ፣ኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ፣መኪኖች፣ሸቶ እና የቤትና የቢሮ እቃዎችም ሳይቀሩ ይሸጡባታል ።
በሚሊዮኖች ስራ አጥ ወጣት ያላት ኢትዮጵያ እንደ ጉድ ሰው አየተጓዘ ከዚህች ትንሽ መንደር የሆነ ነገር ሸምቶ ይሸጥባታል ። ለደርሶ መልስ ትኬት ከ10,000 አስከ 20,000 ብር ለኢትዮጵያ አየር መንገድ በመክፈል በናይፍ በአንድ ክፍል ውስጥ እስከ አምስት አልጋ በሚይዙት አነስተኛ ሆቴሎች ወይንም የእንግዳ ማረፊያ ውስጥ እሰከ አምስት መቶ ብር ድረስ በቀን በመክፈል ይተኛሉ።
ሜሮን ተድላ ( ለደህንነት ሲባል ስሟ የተቀየረ) የዱባይ ነዋሪ ከዱባይ ወደ ኢትዮጵያ ስለተጓዙ የኮሮና ተጠቂዋች እንዲህ ስትል ለፊደል ፖሰት ብላለች;
” እርግጠኛ ባልሆንም እዚህ ዱባይ ነዋሪ የሆነ ኢትዮጵያዊ በቫይረሱ ተይዞ በኢትዮጵያ መንግስት ሪፖርት ውስጥ የገባ አላውቅም ።እዚ አብዛኛው ነዋሪ እረስ በእርስ ስለሚታዋወቅ ኢትዮጵያ ሄዶ ቫይረሱ እንዳለበት የተነገረ ሰው ቢኖር እንሰማ ነበር ።” ትላለች
” የተያዙት አብዛኞቹ ነጋዴዎች ናቸው ።ናይፍ የተጨናነቀች የንግድ ሰፈር ሰለሆነች ፣ኢትዮጵያኖቹም ሲተኙ በተደራራቢ አልጋ ላይ ሆነው አምሰት ወይም አራት ሆነው ስለሆነ ኮሮና ደግሞ አካላዊ ቅርርብን ስለማይፈልግ በቫይረሱ የመያዛቸው እድል የሰፋ ነው ብዬ አምናለው።”
“በአብዛኛው ናይፍ የሚመጡ ኢትዮጵያውያን በኮንቴነር ጭነት የሚነግዱ ሀብታም ነጋዴዎች አይደሉም ።የተወሰነ ሻንጣ ጭነው ሀገራቸው ሲሄዱ ከቀናቸው አስከ ከ50,000 ብር እሰከ 100,000 ብር ድረስ ለማትረፍ የሚጓዙ በሀገር ውስጥ ንግድ ፍቃድ የሌላቸውና አየር በአየር የሚነግዱ ግለሰቦች ናቸው።
” ናይፍን የሚመርጡበት ምክንያት በአቅማቸው አነስ ያለ ብር ከፍለው ቶሎ ገዝቶ ለመሄድ ነው። ናይፍ ላይ ከሶስት ቀን አስከ ሳምንት ቢቆዩ ነው ።” በማለት ናይፍ እንደ ቻይና ውሀን ለኢትዩጵያውያን የኮሮናቫይረስ መለከፍያ ቦታ እንደሆነ ታስረዳለች።
ሰሞኑ የኳታሩ አልጀዚራ እንደዘገበው በናይፍ ቤት ለቤት የኮሮናቫይረስ ምርመራ እንደተጀመረም ዘግቧል።ዩናይትድ አረብ ኤሜሪትስ ከቤት መውጣት ስለከለከለች የንግድ መንደሯ ናይፍም ተዘግታለች በማለት የፃፈ ሲሆን ከዱባይ መንደሮች በናይፍና ዘቅራቢያው ባለ አንድ መንደር ከፍ ያለ የኮሮናቫይረስ ተጠቂ ሊኖር እንደሚችል ዘግቧል።
ሰሞኑን ‘አዲስ አድማስ’ ከተሰኘ ጋዜጣ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ‘ከዱባይና ከሳኡዲ አረቢያ ፣ በርካታ ሺ ኢትዮጵያውያን ለበሽታ በሚያጋልጥ ሁኔታ ወደሀገራችን እየገቡ መሆናቸው፤ ከባድ ስጋት ላይ ጥሎናል እንዲሁም ያለ ምንም የጤና ምርመራ የሚመጡ መሆናቸው ደግሞ አደጋውን እንደሚያከብደው መናገራቸው አሁንም ለንግድ ዱባይ ሄደው ናይፍ ያቀኑት ዜጎቻንን ሪፖርት እንደተደረጉልን ሌሎቹ የዱባይ ተጓዦች በቫይረሱ ተልክፈው ይሆን? ብለን እንድንመረምር ያስገድደናል።