የዛሬ 24 አመት ወደ ኋላ ።የከሸፈው የሆስኒ ሙባረክ የአዲስ አበባ ግድያ ሙከራ ማን አቀናበረው?



በተስፋዬ ጌትነት

ጭጋጋማው ሀምሌ ሰኔ 19,1987 የ67 አመቱን የግብፁን ፕሬዝዳንት በአዲስ አበባ ለመግደል ቀጠሮ ተይዞበታል ። ሰውዬው ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት ( የአሁኑ አፍሪካ ህብረት) አመታዊ ስብሰባ ሲመጡ ግንባራቸውን በጥይት መቶ ገሎ በግብፅ ኢራን መሰል መንግስት እንዲቋቋም ከአፍጋኒስታን ወታደራዊ ስልጠና የወሰዱ ዘጠኝ ግብፃዊያን ሁለት አመት ዝግጅት አድርገዋል። እነዚህ ወጣቶች ሱዳን ካርቱም በሚገኘው አል ጋማ አል ኢስላሚያ ፅንፈኛ ቡድን በመደገፍ ከአፍሪካ አንድነት ስብሰባ ቀደም ብለው ገብተው ከግድያ ቀኑ አራት ቀን አስቀድመው ቦሌ አካባቢ ቤት ተከራይተዋል ።ለመረጃም እንድተጠቅማቸው ከእነሱ አንዱ አንድ ኢትዮጰያዊ ወጣትን እንደሚስትነት ይዟል ።በሱዳን ኤርዌይስና በኢትዮ ሱዳን ድንበር በኩል አውቶማቲክ መሳርያዎች አስገብተዋል። ካርቱም የተዘጋጀላቸው ሐሰተኛ ፓስፓርትም ኢትዮጵያ ለመግባት ወይንም የኢትዮጵያ አየር መንገድ የፍተሻ ሰራተኞችን ለማለፍ አልቸገራቸውም።

የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ሊከፈት የተወሰኑ ሰአት ቀሩት ።ብዙ የአፍሪካ መሪዎች ሸገር ከትመዋል። የመለስ ዜናዊ ደህንነት ያልደረሳባቸው ገዳዮቹ ግብፃዊያን ከአየር ማረፍያው ብዙም የማይርቀው ፍልስጤም ኤምባሲ በተከራዩት ባለ አንድ ፎቅ ቤት ሆነው ሙባረክን ይጠባበቃሉ።
ሆስኒ ሙባረክ የያዘቸው አውሮፓላን ከካይሮ ተነስታ የ3 ሰአት ተኩል በረራ አድርጋ ረፋድ ጠዋት ቦሌ ረገጠች ።ሙባረክ ሁለት አጃቢ መኪኖችን ከፊት አስከትሎ በጥቁሩ መርሴዲዝ ቢንዝ ሊሞዚን መኪና እየጋለበ ሞት ወደተደገሰለት መንገድ ደረሰ ። ከፍልስጤም ኢምባሲ ተቃራኒ አቅጣጫ እንደደረሰ ቡኒ ቫንና ሌላ አንድ መኪና የፕሬዝዳንቱን መንገድ ዘጉት ። ከ70 ሜትር እርቀት ሰባት ሰዎች ሙባረክ ወዳለበት መኪና የተኩስ እሩምታ ማውረድ ጀመሩ ።ሁለት ሰዎች ከባለ አንድ ፎቅ ቪላ ቤት ላይ ሆነው ወደ ሙባረክ መተኮሱን ተያያዙት ።ጩሀት ትርምስ ተፈጠረ ።አዲስ አበባ የውጪ መሪ ከተገደለባት ጉድ ሊፈላባት፣ እንግዳ ተቀባይነቷ አፈር ሊልስ ሆነ።ለሙባረክ ጥበቃ የተመደቡ የኢትዮጵያ ፓሊሶችና ደህንነቶች ግራ ገባቸው ። ከተተኮሱት ጥይቶች አንድ ቀለሀ ብቻ ነው የሙባረክን መኪና መስኮት ለመብሳት የመጣችው ። ሎሎች የከሸፉ ነበሩ። የተኩሱ ትእይንት ቀጠለ ።ሁለት ኢትዮጵያዉያን ፓሊስ ተገደሉ። ጠቆረ ያለ ሱፍ አርጎ የአፍሪካ የመሪዎች ስብሰባ መክፈቻ ላይ የመጣው ሙባረክ ግራ ቢጋባም ጉዳት ሊደርስበት እንደማይችል እርግጠኛ ነው። ምክንያቱም የነበረበት መኪና ጥይት አይበሳውም ። ከገዳዮችም መሀከል ሁለት ግብፃዊያንም ተገደሉ።የኢትዮጵያ ፓሊሶችም ወደ ፎቁ ቤት ተኮሱ።ወደ ቤቱ ሲዘልቁም ተቀጣጣይ ፈንጆች ።ሽጉጦች እና ረዘም ያሉ ጠመንጃዎችን አገኙ።
ከአዲስ አበባው ግድያ በፊት ሁለት የግድያ ሙከራዎች የከሸፈባቸው ሙባረክ ይዟቸው የመጧቸውን ጋዜጠኞችና ፎቶ ግራፈሮችን ይዘው ወደ ካይሮ ፈረጠጡ። ካይሮም እንደደረሱ ልጆቻቸው በለቅሶ ተቀበሏቸው ። ሙባረክም እንዲህ አሉ ” ከሞት አደጋ ሰለተረፍኩ ፈጣሪን አመሰግናለው ። ፈጣሪ ከክፉ ነገር እንደሚጠብቀኝ አምናለው። የተኮሱብኝን ሰዎች አይቻቸዋለው ።ሁለቱ ከፎቅ ጣሪያ ላይ ነበሩ ።ሌሎቹ ከመኪኖቹ ላይ ።ተኳሾቹ በፍፁም ኢትዮጵያዊ እንዳልሆኑ አርግጠኛ ነኝ ። ሱዳን የሚገኘው ፅንፈኛ ኢስላማዊ ቡድን መሪ ሀሰን ቱራቢ ነው እነዚህን ገዳዮች ያደራጀብኝ” ብለው አሰተያየት ሰጡ።
ሙባረክ እስራኤል ጋር ጥሩ ወዳጅነት ፈጥረው ስለነበረ የወቅቱ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ኢሳቅ ራቢንም ” በተደረገብክ የግድያ ሙከራ ሁሉም እስራኤላዊ አዝኗል። እንኳን ተረፍክልን ።አንተ ጥሩ ወዳጃችን ነክ ዘወትርም መልካም ነገር የምንመኝልክ ሰው ነክ ” ብለዋቸው ነበር ።

ከአምስት ቀን በኋላ ስለሁኔታው ማብራሪያ የሰጠው የኢትዮጵያ ሬድዮ አምስት ግብፃዊያን እንደተገደሉ አንደኛው አቀነባሪ ከሀገር እንዳመለጠ ተናግሮ ግድያውን ያቀናበሩት ሰዎች ግን ሱዳን እንዳሉ አስደምጧል።
የከፍተኛው ፍርድ ቤትም በግድያው ተሳትፈዋል ያላቸውን ሶስት ግብፃዊያን; አብዱል ጋሊ፣ሰኢድ ሙሀመድ እና አህመድን ኢልናዲን የሞት ፍርድ ወስኖባቸው በወቅቱ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ለነበሩት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ የሞት ፍርዱን እንዲያፀድቁ ልኳል። የሞት ፍርዱ ይፈፀም አይፈፀም የጠራ መረጃ እስከ አሁን የለም።
ግብፅ በአሸባሪዎች ላይ ጠንካራ እርምጃ ስለወሰድኩኝ በዚህም የተቆጣው በሱዳን ተቀምጦ ሚረብሸኝ አክራራዊ ሙስጠፋ ሀማዝ ነው የግድያውን ሴራ ያቀነባበረው ብትልም ኋላ ግን ሀማዝ በወንጀሉ የለበትም ብላለች ።
የኢትዮጰያ መንግስትም ሱዳን ያሉ አክራሪ ሀይሎች ናቸው ብሎ ለተባበበሩት መንግስታት የፀጥታ ቋሚ ኮሚቴ ቅሬታ ቢያሰማም ሱዳን እኔ የለውበትም ብላ መለሰች ።ይሄም ጉዳይ በጊዜው በሱዳንና በኢትዮጵያን ግንኙነትን ላይ ጥላሸት አጠልሽቶ የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊና አሁን ከስልጣን ወርደው እስር ቤት የሚገኙትን የሱዳን ፕሬዝዳንት ኦማር አልበሽርን ሆድና ጀርባ እንዲሆኑ አድርጎ ነበር።



የግብፅ የመንግስት ሚዲያዎች ትናንት በለቀቁት ዜና ግብፅን ከአንዋር ሳዳት ግድያ በኋላ ተቀበልው ለ30 አመት የመሩትና ከዘጠኝ አመት በፊት በተነሳው የግብፅ አብዮት ከስልጣን የወረዱት ሆስኒ ሙባረክ የቀዶ ጥገና ካረጉበት ካይሮ በሚገኝ ሆስፒታል በ91 አመታቸው ዛሬ ማረፋቸው ተነግሯል። ስልጣን ከመያዛቸው በፊት ሙባረክ የጦር ጀት አብራሪ የነበሩ ሲሆኑ አላ እና ገማል የተባሉ ሀለት ልጆቹም ሱዛና ሙባረክ ከተባለች ግማሽ እንግሊዚያዊ ዜግነት ካላት ዶክተር ወልደዋል ። የአልኮልም ሆነ የሲጋራ ሱስ ያልነበራቸው ሙባረክ ከስልጣን ይውረዱ ተብሎ በተነሳባቸው ተቃውሞ ለተቃውሞ የወጡትን ግብፃውያን በፀጥታ ሀይሎች አስገድለዋል ተብሎ የእድሜ ልክ አስራት ቢፈረድባቸውም ከሶስት አመት በፊት ከእስር የተለቀቁት ።ከእስር ቤት ከወጡም በኋላ ብዙውን ግዜ ካይሮ በሚገኘው ወታደሪዊ ሆስፒታል ነበር ያሳለፉት ።ህክምናቸውን ሲከታተሉ ትናንት ጠዋት በሒወት ተለይተዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *