ራይድ ትራንስፖርት ቴክኖሎጂ መስራች ወይዘሪት ሳምራዊት ፍቅሩ በኢትዮጵያ በስራ ፈጣሪነት ከመትጠራ ግለሰብ መሀል ናት ። ማታ ስራ አምሽታ በአቅራቢያዋ ያለን ታክሲን ማግኘት መቸገሯ ።ብልሀት አስገኝሎታል ። ለምን በስልክ ወይም በሞባይል አፕ በአቅራቢያ ያለ ትራስንፖርት መኪና አልፈጥርም ብላ ያስተዋወቀችው ቴክኖሎጂ ዛሬ በአዲስ አበባ የታወቀ ስራ ሆኗል ።ሰዎች ሲቸኩሉ ” ራይድ ልጥራ ” በማለት 8294 አቅራቢያቸው ያለን መኪናን መጥራት የተለመደ ነገር ሆኗል።
የፊደል ፖስት ዋና አዘጋጅ ተስፋዬ ጌትነት የራይድ ትራንስፖርት አጠቃላይ እንቅስቃሴ ምን ይመስላል በሚል ጉዳይ ላይ ወ/ሪት ሳምራዊት ፍቅሩን ጠይቆ ያገኘው ምላሽ ከታች ያለውን ይመስላል;
ፊደል ፖስት: ራይድ ትራንስፖርት ቴክኖሎጂን በአዲስ አበባ በማስጀመርሽ አመጣሁት ብለሽ የምትነግሪን ስኬት ካለ?
ሳምራዊት: ስኬት በብዙ ነገር ይገለፃል ። ለምሳሌ ያክል የአንድ ቢዝነስ ስኬት ከሚገለፅባቸው ነገሮች መሀል የሚያቃለው ችግር ፣የሚፈጠረው ስራ እድልና ገቢ እንዲሁም የሀገሪቷ ኢኮኖሚ ላይ የራሱ የሆነ ተፅእኖ ማድረግ ይገኝበታል ። ራይድ ትራንስፖርት ሰው ለራሱ የሚጠቅማባቸውን መኪኖች በከተማው 2.4 ሚልየን ህዝብ ትራንስፖርት ችግር አለበት የተባለውን ማህበረሰብ እንዲያገለግል አድርጓል ። አንድ ቦታ ለመድረስ ፈልገክ በአቅራቢያ ያለ መኪናን በራይድ አፖ ወይም በጥሪ ማዕከላችን ቁጥር 8294 ደውለክ በደቂቃዎች በተመጣጠነ ዋጋ ማግኘት ትልቅ ነገር ነው ። የሚመጣልክን መኪና ታርጋ የሹፌሩን ስልክና ስም ማወቅ ደግሞ ለደህነንነትክ ትልቅ ፋይዳ አለው።
አስበው !አጠገብክ ልትወልድ የደረሰች ሴት በአጣዳፊ ሆስፒታል መውሰድ ቢኖርብክ መንገድ ወጥተክ መኪና አስክትፈልግ ምትፈጀውን ግዜ ? ራይድ ለዚህ መልስ ይዞ መምጣቱ ትልቅ ነገር ነው ። በነገራችን ላይ ማህበራዊ ግዴታችንን ለመወጣት ነፍሰጡር ሴቶች ለመውለድ ጤና ተቋም ሲሄዱ ነፃ ትራንስፖርት ነው ምናቀርበው ።በዚህም ብዙ ሰው አገልግለናል ።
ከስራ እድል ፈጠራ በኩል በትንሽ ሰዎች የጀመርነው ዛሬ ከ20,000 መኪኖች በላይ ከእኛ ጋር ይሰራሉ ። አስብ በሹፌሮቹ ስር የሚተዳደረውን ቤተሰብ ካሰብክ ደግሞ በራይድ ገቢ የሚጠቀመው ከመቶ ሺ ሰው ይበልጣል። ለአንድ ሰው ወይንም ቤተሰብ ይጠቅሙ የነበሩ መኪኖችን ስበን አምጥተን ህብረተሰቡን እየጠቀሙ ሰዎች ገቢ አንዲያገኙ አድረገናል ።ቆሞ የነበረ ሀብት ወደ ገቢነት ወደ አገልግሎት ቀይረናል ።ኢትዮጵያ እኮ ብዙ ሀብቶች አሉሏት ።ወደ ገንዘብ ልንቀይራቸው ስራ እድል ልንፈጥራባቸው የምንችል ። ራይድ ለዚህ አንድ ትንሹ ማሳያ ነው ።ብዙ ነገር ቢቀረንም።
ከኢኮኖሚ አንፃር በሚልየኖች የሚቆጠር ግብር ለመንግስት እንከፍላለን። ይሄ ደግሞ ለሀገር የምናስገኘው ገቢ ነው ።በዚህም ደስ ይለናል።
ፊደል ፖስት: መጋቢት 4,2012 ኢትዮጵያ የገባው የኮሮናቫይረስ እሰከ አሁን 1,000 ገደማ ሰው ሲያሳጣን ከ60,000 በላይ ሰው በቫይረሱ አሰይዞብናል ።በራይድ ትራንስፖርት ላይ ያሰደረው ተፅዕኖ አለ?
ሳምራዊት: ቫይረሱ ሀገር ኢኮኖሚ ላይ ያሳደረው ተፅእኖ እውን ነው ።የሀገር ኢኮኖሚ ሲቀዘቅዝ አንደማንኛወም ቢዝነስ የእኛም ቢዝነስ ይነካል ። ቫይረሱ ኢትዮጵያ አንደተከሰተ የራይድ ትራንስፖርት ስራ ቀዝቅዞ ነበር ። ትንሽ ጊዜ ከቆየ በኋላ አሁን እንደ ድሮ በሚባል ደረጃ ተመልሷል ።
ፊደል ፖስት: ራይድ ትራንስፖርትን የሚያሰተዳድረውና አንቺ በኃላፊነት የምትመሪው ኃይብሪድ ዲዛየን ለኮሮናቫይረስ ለመዋጋት ለሚደረገው ስራ በሚለየን የሚቆጠር ብር አንደአወጣቹ ሰምቻለው ።ዘርዘር አርገሽ ንገሪን እስቲ?
ሳምራዊት: ሀገርክ ላይ አደጋ ሲጋረጥ የምትችለውን በአቅምም በጉልበትም መርዳት አለብክ ። ኮሮና ሲከሰት አብዛኛው ስራችን ድጋፍ የማድረግ ስራ ላይ ማተኮር ነበር። ከራይድ ቤተሰቦች ጋር በመተባበር ወደ ዘጠኝ ሚልዮን ብር የሚጠጋ ድጋፍ አድረገናል ።ለነርሶችና ለዶክተሮች የአፍ ጭንብልና ጓንት ለመስጠት አንስቶ በከተማዋ ሳኒታይዘር የአፍ ጭንብልና ጓንት የማደል ስራ ላይ ተሳትፈናል ።ይሄ ስራችን የሚቀጥል ይሆናል።
ፊደል ፖስት ። የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ችግኝ ተከላ ጥሪን በተመለከተ መልካም ስራ እንደሰራቹ ይነገራል ። እስከአሁን ያላቹ እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?
ሳምራዊት: የጠቅላይ ሚኒስትሩ የአረንጓዴ አሻራ ፕሮጀክት የችግኝ ተከላ ስራ ስላመንበት ወዲያው ነበር የተቀላቀልነው ። ። ከባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር ገላን አካባቢ ቦታ ተሰጠን ።እዚያም ወደ አስር ሺ የዛፍ ችግኞችን ተክለናል። አምና የዛፍ ችግኝ ብቻ ነበር የተከልነው ።ዘንድሮ አቮካዶ ፣ዘይቱን እና የመሳሰሉትን የፍራፍሬ ተክሎችን ተክለናል ።ቦታውን አጥረን ወደ አስራ ሁለት ሰራተኛ ቀጥረን ቤት ፣ቢሮ እና፣መጋዘን እዛው ሰርተልነናቸው ፣ውሃ አሰገብተን አየተንከባከብን እንገኛለን ። ጥሩ ደረጃ ላይም ይገኛል

ፊደል ፖስት: ኡበርን የመሳሰሉ ትላልቅ የአሜሪካ የታክሲ ሄይሊንግ ትራንስፖርቶች ምግብ ለሰዎች የማጓጓዝና የማስረከብ ስራዎች ላይ ሲሰሩ ይስተዋላል ራይድ ትራንስፖርት የዚህ አይነት አላማ የለውም?
ሳምራዊት: እውነት ለመናገር የትራንስፖርት ስራው እራሱ ሰፊ ነው ።በእርግጥ በዚህ ሁሌ እንወሰናለን ማለት አይደለም ።ብዙ እቅዶች አሉን ።ሲያልቁ ለመስራት ስንጀምር የምንናገራቸው ።ባልደራሱ የተባለ እህት ኩባንያ አለን እሱ እቃዎችን የማጓጓዝና የማስረከብ ስራዎች አሁን እየሰራ ይገኛል።
ፊደል ፖስት: የራይድን ትራንስፖርት ተጠቃሚዎች ከሚያነሷቸው ችግሮች መሀል ኦፕሬተሮች ጋር ስልክ ሲደወል አልፎ አልፎ አይነሳም ይላል ።ችግሩን ለመቅረፍ ምን እየሰራቹ ነው ።
ሳምራዊት: የስልክ አለመነሳቱ ችግር የኦፕሬተሮች ጋር ሳይሆን የኢንተርኔት መቆራረጥ ነው ። ኢንተርኔት በመሀል ሲቆም የስልክ ሲስተማችን ለአስር ደቂቃ ወደ ስራ አይገባም ። ይሄን ችግር ለመቅረፍ ከቴሌ ጋር እየሰራን ነው። እሰከመስቀል በአል ድረስ ይፈታል ብለናል ። ኦፕሬተሮች ብዙ ቀጥረናል።የኦፕሬተሮች እጥረት የለብንም ። እንደውም አሁን ባለው ኮሮና ብዙ ድርጅቶች ሰራተኛ ሲቀንሱ እኛ አየቀጠረን ነበር ።
ፊደል ፖስት: የራይድ ትራንሰፖርት ባሻገር ሌሎችም በተመሳሳይ ዘርፍ ገብተው አየሰሩ ከእናንተ ጋር መወዳደደር አየጀመሩ ነው። ይሄን አንዴት ታዩታላቹ ?
ሳምራዊት: በደስታ ነው የምናየው ።ወድድር ሲኖር ትበረታለክ ።እራስክን የተሻለ ለማድረግ አንደ አንድ ስንቅ ይሆንካል ። ገና በቴክኖሎጂ ምን ተሰራና! ብዙ ብዙ ስራዎች ይቀሩናል ። እኔ እንደግለሰብ እኔ የምሰራውን ስራ ሌላ ሰው ገብቶ ሲወዳደር ደስ ይለኛል ።ውድድሩ አንዱን ጠልፎ ለመጣል አይሁን እንጂ! ።በተሻለ ሀሳብ በተሻለ ስራ ከሆነ እኛም የምንበረታበት የምንሻሻልበት ጤነኛ ውድድር ይሆናል ።
ፊደል ፖስት ።የራይድ ትራንስፖርት አይነት ስራ የሚሰሩ መኪኖች በአዲስ አበባ በዙ የሚሉ ሰዎች አየተስተዋሉ ነው ይሄን አንዴት ታይዋለሽ?
ሳምራዊት: በዛ ብዬ አላምንም ። አዲስ አበባ ከሁለት ሚልየን ህዝብ በላይ ትራንስፖርት ይቸገራል ። በእርግጥ አዲስ የትራንሰፖርት አገልግሎት ራይድ በሚሰጣቸው አገልግሎት በዛ ብሎ የመታየት ነገር ይኖራል ።ነገር ግን ትራንስፖርት ስንል ባስ ፣ሚኒ ባስ ፣መሀከለኛ ባሶችን ሁሉ ይጨምራል ።በእዚህ በኩል ብዙ ስራ መስራት ይጠበቅብናል።
ፊደል ፖስት: ራይድ ታክሲ ነን በሚሉ ሰዎች ዝርፊያ ሲፈፀም እናያለን ። ይሄን ለመዋጋት ምን እያደረጋቹ ነው?
ተጠቃሚዎችን በተደጋጋሚ እየነገርን ያለው ነገር ቢኖር ።ከሲስተም ውጪ ራይድ ነን በሚሉ መኪኖች እንዳይጠቀሙ ነው ። በሲስተም ሰትጠቀም የሹፊሩ አድራሻ እኛ ጋር ስለሚኖር ወንጀል ቢፈፀምብክ ወዲያው ይገኛል ። እኛ ሲስተም ላይ ሳይኖሩ ስቲከር እየለጠፉ ራይድ ነን በሚሉ ሰዎች እንዳይታለል ።በእነደዚህ አይነት ሰዎች ወንጀል ቢደርስበትም እኛ ልንረዳ የምንችልበት ምንም ምክንያት የለም ።እኛ ጋር ሲስተም ላይ ሳይኖሩ “ራይድ ነን ” በሚሉት እርምጃ ለመውሰድ ከፖሊስ ጋር እየሰራን ነው። የራይድ ሹፊሮችን በተመለከተ ‘ዱካ’ የተሰኘ የአደጋ ማሳወቂያ መተግበሪያ ሥራ ላይ አውለናል።የራይድ ትራንስፓርትን በስራ ላይ እያሉ ዘረፋ ወይንም አደጋ ቢደርስባቸው ለፓሊስ፣ አቅራቢያቸው ላለ ማህበረሰብ እንዲሁም በቅርበት ላሉ ሎሎች የራይድ ታክሲ ሹፌሮች በስልክ ጥሪ የሚያሳውቅ ነው ይሄ ሶፍትዌር።። በተጨማሪ የመኪና ጎዞ ክትትል፣የፍጥነት መቆጣጠርያ ጠቋሚ፣የነዳጅና የመኪና ወጪ መከታተያ፣የስራ፣ክልል መገደቢያ፣የኮሮኮንች ላይ መኪና መናጥን ይጠቁማል ሶፍትዌሩ ይጠቁማል።
ፊደል ፖስት: አቶዝን የመሰሉ ትናንሽ መኪኖች በእናንተ ስራ ላይ ይታያሉ። ይሄ ለምን ሆነ?
ያለውን የትራንስፖርት ችግር አይተን ነው ያስገባናቸው ።በእርግጥ ከሀምሌ መጀመሪያ ጀምሮ መቀበል አቁመናል ።ያሉትም ትንሽ ሰርተው በሌላ መኪና ካልቀየሩ አገልግሎቱን ከእኛ ጋር ሆነው መስራት አይችሉም።

ፊደል ፖስት: የራይድ ቤተሰቦች በአዲሱ አመት ከእናንተ ምን ይጠብቁ?
ሳምራዊት: የእኛ የሁልግዜም ስጦታ ተጠቃሚዎች ካሰቡበት ቦታ በግዜዉ ቶሎ እንዲደርሱ ማደረግ ነው። ራይድን ለሚጠቀሙ ደንበኞች ሆነ ለራይድ ቤተሰቦች የተለያየ ጥቅም የሚያገኙበት አዳዲስ ፓኬጆች አዘጋጅተናል ።እሱን በአጭር ወራት ውስጥ እናሳውቃለን።
ፊደል ፖስት: መጨመር ምትፈልጊው ነገር ካለ?
ሳምራዊት: የራይድ ቤተሰቦችን ሁሉንም የኢትዮጵያ ህዝብ አዲሱ አመት የሰላም የብልፅግና አንዲሆን እመኛለው።