ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በአዲስ አበባ የኔትወርክ አገልግሎቱን መስጠት ጀመረ

በኢትዮጵያ ዙሪያ በሚገኙ ዐስር ከተሞች የደንበኞች የኔትወርክ ሙከራውን ያካሄደው ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በአዲስ አበባ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን በዛሬው ዕለት በሀያት ሪጀንሲ ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል።

በተጨማሪም ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ አገራዊ የአገልግሎት ማስጀመሪያ ዝግጅቱን ዛሬ ማታ ከ12፡00 እስከ 1፡30 በወዳጅነት ፓርክ እንደሚያካሂድ የገለጸ ሲሆን፤ በዚሁ ዝግጅት ላይ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎች፣ የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ባለአክሲዮኖች፣ የአጋር ድርጅቶች እና የሌሎች ባለድርሻ አካላት ተወካዮች እንደሚታደሙበት ተነግሯል።

የአዲስ አበባ ዐ7 ኔትወርክ ደንበኞች የ4G ዳታ፣ የድምፅ ጥሪ እና የጽሁፍ መልዕክት አገልግሎቶችን ከሳፋሪኮም ኢትዮጵያ እና ከኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞች ጋር መለዋወጥ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ጥሪዎችን ማድረግ እንደሚችሉ የተገለጸ ሲሆን፤ ደንበኞች ተመጣጣኝ ዋጋ ያላቸው የስልክ ቀፎዎችንም መግዛት ይቻላሉ ተብሏል።

የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ መለያ በተለጠፈባቸው ጋራድ ሞል፣ መስቀል ፍላወር፣ ጀሞ፣ ቦሌ (ሰላም ሲቲ ሞል ፊት ለፊት) እና ሲኤምሲ (ጋስት ሞል ጎን) በሚገኙ መደብሮቻችን እና ሌሎች በከተማው ውስጥ በሚገኙ የሳፋሪኮም መለያ በተለጠፈባቸው ሱቆች ደንበኞች የስልክ ቁጥሮቻቸውን መምረጥ፣ ሲም ካርድ መግዛት፣ አየር ሰዓት መግዛት እና የደንበኞች ድጋፍ ማግኘት እንደሚችሉም ሳፋሪኮም አስታውቋል።

ደንበኞች 700 ላይ በመደወል የሳፋሪኮም የጥሪ ማዕከልን ማግኘት የሚችሉ ሲሆን፤ አገልግሎቶቹም በ5 ቋንቋዎች (አማርኛ፣ ኦሮሚኛ፣ ሱማሊኛ፣ ትግሪኛ እና እንግሊዝኛ) የሚሰጡ ይሆናል ተብሏል።

የሳፋሪኮም ኔትወርክ በአሁኑ ጊዜ በድሬዳዋ፣ ሐረር፣ ሐረማያ፣ አዳማ፣ ባህር ዳር፣ ቢሾፍቱ፣ ሞጆ፣ ደብረ ብርሃን፣ አወዳይ፣ ጎንደር እና አዲስ አበባ የሚገኝ ሲሆን፤ አገራዊ ኔትወርክ ማስጀመሪያው ቀጥሎ እስከ ሚያዝያ 2015 ድረስ ተጨማሪ 14 ከተሞችን እንደሚያዳርስም አስታውቋል።

“አገልግሎታችንን በአዲስ አበባ በመጀመራችን እና አገራዊ አገልግሎት ማስጀመሪያ ዝግጅታችንን ለማካሔድ በመብቃታችን የተሰማን ደስታ ከፍተኛ ነው” ያሉት የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አንዋር ሱሳ፤ “በኹለገብ የቴሌኮም አገልግሎት ፈቃዳች ግዴታዎች መሠረት የከተማ በከተማ የደንበኞች ሙከራዎቻችንን የምንቀጥል ይሆናል” ሲሉ ተናግረዋል።

አክለውም፤ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ለተጨማሪ ከተሞች እና የተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች የኔትወርክ አገልግሎቱን ማቅረብ እንደሚቀጥል ገልጸው፤ “ኹሉንም ኢትዮጵያዊያን ለማገልገል እና ለአገራችን ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን የበኩላችንን አስተዋጽኦ ለማድረግ እየተዘጋጀን ባለንበት በዚህ ጊዜ፤ መንግሥት፣ ባለድርሻ አካላት እና አጋር ድርጅቶች ላደረጉልን መጠነ ሰፊ ድጋፍ ከፍተኛ ምስጋናዬን አቀርባለሁ” ብለዋል።

የሳፋሪኮም ኃ.የተ.የግ.ኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፒተር ንዴግዋ በበኩላቸው “ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥራት ባላቸው የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎቶች የኢትዮጵያን ሕዝብ ለማገልገል እድሉን ስላገኘ እጅጉን ደስተኛ ነኝ” ብለዋል።

አክለውም “እያቀረብን ያለነው ቴክኖሎጂ ለመጪው ዲጂታል ጊዜ ብሎም የሰዎችን ሕይወት በዲጂታል መፍትሔዎች ለመቀየር አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ባለሙሉ ተስፋ ነን።” ሲሉ ገልፀዋል።

የቮዳኮም ግሩም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሻሚል ጆሱብ በበኩላቸው፤ እያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ ከዓለም አቀፉ ዲጂታል ኢኮኖሚ ጋር ለማገናኘት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ተሳታፊ ለነበሩት የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ አመራሮች፣ ሠራተኞች እና አጋሮች በሙሉ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኔትወርክ በኹሉም ቦታ መገኘት ቴክኖሎጂን ለበጎ የሚያውሉ አገልግሎቶችን በጤና፣ በትምህርት፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በግብርና እና በዲጂታል ፋይናንስ ተደራሽ በማድረግ የመላ ኢትዮጵያዊያንን ሕይወት በአዎንታዊ ሁኔታ የሚቀይረው ይሆናል::” ሲሉም ሻሚል ጆሱብ ተናግረዋል።

ኢትዮ ንግድ ኢንቨስትመንት

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *